አዲስ አበባን በአዲስ የተስፋ ብርሃን!!

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን ይመኛል፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ኢንቨስተርስ ሪሌሽን፣ የሚዲያ ፕሮዳክሽን እና ሁነት ዝግጅትን በአንድ መዕቀፍ ይዞ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ ብቸኛ ተቋም የሆነው ግዙፉ ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ኃ/የተ/የግል ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የተሰየሙትን ልዩ ልዩ የጳጉሜ ቀናት መርሃግብሮች እና የእንቁጣጣሽን ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያስተባበረ ይገኛል፡፡

ጳጉሜን አንድ የይቅርታ ቀን!

ክብርት ም/ከንቲባዋ በተገኙበት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የቀድሞ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች በሚገኙበት በሸራተን አዲስ ሆቴል ልዩ የይቅርታ መጠየቅ ሥነ-ሥርዓት ይከወናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ ህዝብ አገልጋዮች መንግስት ላሳየው የአስተዳደር ጉድለት ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡  

በከሰዓት ፕሮግራም ደግሞ ሴቶች፣ ህጻናት፣ የኪነ-ጥበብና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች በመንግስት ወይም በግል ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ አረጋዊያንን ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት የአረጋዊያንን ጉልበት መሳምና እግር ማጠብ የሚከወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

ጳጉሜን ኹለት! የአብሮነት ቀን!

ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ፣ ዘመንና ፈተና ያልሻረው የኢትዮያዊያን የአብሮነት ታሪክ የሚገለጥበት ልዩ ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡ በመላ ከተማዋ ሸገር ዳቦን የሚያከፋፍሉ ሱቆች በሙሉ አቅም ለሌላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዳቦ በነጻ ያድላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቅመ ደካሞችን፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውንና በልዩ ልዩ ችግር ያሉ ዜጎችን ለማበረታታት የቤት ለቤት ጉብኝት ከመካሄዱም በተጨማሪ ለወቅታዊው ወረርሽኝ ሲባል በለይቶ ማቆያ ያሉ ዜጎችን መጎብኘት የፕሮግራሙ አካል ይሆናል፡፡

ጳጉሜን ሶስት የአምባሰደርነት ቀን!

ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪዎች ለከተማቸው አምባሳደሮች መሆናቸውን የሚያንጸባርቁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በዕለቱ የሚከናወኑ ሲሆን በአዲስ አበባ መኖሪያቸውን ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የመልካም በዓል ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህ ዕለት ክብርት ም/ከንቲባዋ በጊዚያዊው አትክልት ተራ (ጃንሜዳ) በመገኘት ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመጠበቅ የሚያግዙ የንጽህና እና ጥንቃቄ ቁሳቁሶችን ለህብረተሰቡ ያድላሉ፡፡

ጳጉሜን አራት የምስጋና ቀን!

የኢትዮጵያዊያን የሆነው ነባሩ መመሰጋገንን የሚያስታውሱ ልዩ ልዩ ክንውኖች ለዕለቱ ተይዘዋል፡፡ ለአዲስ ዓመት ዝግጅት አቅም ለሌላቸው ዜጎች ድጋፍ ማሰባሰብ፣ ድጋፍ ማድረግና ድጋፍ ላደረጉም ምስጋናን መለገስ በምስጋና ቀን የሚከወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ በዕለቱ በዋናነት ሊመሰገኑ የሚገባቸው በተለያዩ ሞያዎች ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይመሰገናሉ፡፡

ጳጉሜን አምስት የብሩህ ተስፋ ብስራት ቀን

ሀገራችን እና ህዝቦቿ ያሳለፉትን ለወራት የዘለቀ የፈተና እና የድብርት ስሜት አራግፈው አዲስ ተስፋን እንዲሰንቁ የሚያነሳሱ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት እለት ጳጉሜ አምስት ይሆናል፡፡ ዕለቱም የብሩህ ተስፋ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን የአዲስ ዓመት ዋዜማ እንደመሆኑ በዕለቱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከናወናሉ፡፡ አዲስ ዘመን መምጣቱን የሚያበስሩ መልዕክቶችን የያዙ የፖሊስ ማርሽ ባንድ አባላት በከተማዋ እየተዘዋወሩ የሚያሰሙት ጣዕመ ዜማ የዝግጅቱ አካል ከመሆኑም በተጨማሪ በሆስፒታሎች እና በቀድሞ ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች በመዘዋወር የእንኳን አደረሳችሁ መልክቶች ይተላለፋሉ፡፡

መስከረም አንድ አዲስ ዓመት

የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች በሚሳተፉበት ክብርት ም/ከንቲባዋ አንድ መቶ ለሚሆኑ አቅመ ደካችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የምሳ ግብዣ ያደርጋሉ፡፡

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የማስተዋወቅ፣ ሁነቱን የመሰነድ እና የማስተባበር ሥራዎችን በብቁ ባለሙያዎችና የዘመኑ መሣሪያዎች በመታገዝ ይሠራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የሚከበሩትን ተከታታይ ቀኖች ስኬታማ እና ደማቅ እንዲሆኑ ልዩ ልዩ ህትመቶችንና የህትመት ዲዛይኖችን ይሰራል፤ እያንዳንዱን ዕለትና ሁነቶች የሙያ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በድምጽና ምስል ይሰንዳል! ለሁነቶቹ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ መጠን ያላቸውን መድረክና የድምጽ መሳሪያዎችና ሌሎች የቁሳቁስና የሎጀስቲክስ አቅርቦት ያከናውናል፡፡  

                                         እንኳን አደረሳችሁ!

                                     በመልካም አዲስ ዓመት!

ነሀሴ 29, 2012 ዓ.ም.

ዳያስፖራው 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ

ዳያስፖራው ባለፉት 10 ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደሚናገሩት ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ለምትገነባው ግድብ በቦንድ ግዢና በስጦታ እየደገፈ ነው።

 

መንግሥት የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የወሰዳቸው እርምጃዎችና የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ዳያስፖራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠረ ተናግረዋል። በአጠቃላይ ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ባለፉት 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ በቦንድ ግዢና ስጦታ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

 

ኢዜአ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት የተካሄደ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የፈጠረው መነቃቃት በ2013 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል። በዚህ በጀት ዓመት እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው ገንዘብ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

መጋቢት 22, 2013 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ኢ-ፍትሐዊ ጫና ለመታገል መወሰን!

በላስ ቬጋስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባደረጉት ሰልፍ የህወሃት ቡድን የፈፀመውን የሰላም ማደፍረስ እና የክህደት ወንጀል አውግዘዋል። በሕወሃት ስርዓት ተጠቃሚ በሆኑ የዳያስፖራ ቡድን አባላት ግፊት በኢትዮጵያ ላይ በአንዳንድ የአሜሪካ የሕግ አውጪ እና የሕግ አስፈፃሚ አካላት የሚደረገውን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ተቃውመዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ ለሀገራቸው እና ለመንግሥት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። በዲፕሎማሲው ረገድ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ኢ-ፍትሐዊ ጫና በተደራጀ መንገድ ለመቋቋምና ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ለመታገል መወሰናቸውን አረጋግጠዋል። ሰልፈኞቹ የጁንታው ቡድን እና ተባባሪዎቹ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀሙትን አሰቃቂ ወንጀሎች በማውገዝ፣ አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን በጥንቃቄ በመመርመር ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥሪ የሚያቀርቡ እና ሌሎችም መልዕክቶችንም አስተላልፈዋል።

ሰልፈኞቹ ጥያቄያቸውን በኔቫዳ ግዛት ተመራጭ ለሆኑ ሁለት ሴናተሮች እና አራት የኮንግረስ አባላት በጽሑፍ አቅርበዋል።

 

በሰልፉ ሥነ-ሥርዓት ላይ በርካታ የላስቬጋስ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል። ሰልፉን በላስ ቬጋስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እና የላስ ቬጋስ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ንዑስ ቡድን አባላት ማስተባበራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል። (አብመድ)

መጋቢት9, 2013 ዓ.ም.

በአማራ ክልል ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ ለሚ ናሽናል የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡

ለፋብሪካ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርአት እየተከናወነ ነው፡፡የሲሚንቶ ፋብሪካው በለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የሚገነባ ሲሆን 270 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡  ፋብሪካው በመጀመሪያው ዙር ግንባታው 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል ተብሏል፡፡ ዘገባው የኤፍ ቢሲ ነው፡፡

 

የካቲት 25, 2013 ዓ.ም.

የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፓኬጅ ለዳያስፖራ

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ የሚኖሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዳያስፖራዎች የሚሳተፉባቸው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች እንደሚያዘጋጅ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው የብድር አማራጭ ከሚያመቻቹ ባንኮች እና የቢዝነስ ሐሳብ ካላቸው የመንግሥት አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቋማት ጋር ምክክር አድርጓል።

ምክክሩ በዋናነት አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው እና በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች በአነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በአገራዊ የልማት ሥራዎች በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው መሆኑን ተናግረዋል። ገቢያቸው አነስተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታበከፍተኛሁኔታመሳተፋቸውንገልጸዋል።

ይህ የሚያሳየው ከብዛታቸው አንጻር ብዙ ሀብት መኖሩንና በአንድ ላይ በማሰባሰብ በፓኬጅ ቢደራጁ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት እንደሚያመጡ ነው ብለዋል። በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሊቀርብላቸው እና እነሱን የሚመጥኑ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።የፓኬጁ መዘጋጀት ዳያስፖራዎቹ ያካበቱትን ገንዘብ እና ልምድ ለአገራቸው እድገት እንዲያውሉት እና ሀብታቸውም እንዳይባክን ይረዳል ብለዋል-ዋና ዳይሬክተሯ። የዜና ማንጭ ኢቢሲ

የካቲት 4, 2013 ዓ.ም.

በትግራይ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው!

በትግራይ ክልል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡ የጤና ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የጤና ሚንስቴር እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመሆን የቀን ተቀን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ መድሀኒቶችን እና የሕክምና መገልገያዎችን የሚያሰራጩ የመቀሌ እና የሽሬ የመድሀኒት አቅርቦት ቅርንጫፎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በክልሉ የሚገኙ የደም ባንኮች ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በነዚህ ባንኮች ለማይሸፈኑ ፍላጎቶች ከማዕከል ደም እየተላከ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል የመድሀኒትና ግብአት ስርጭት ተደርጎ ወደ ስራ የገቡ ጤና ተቋማት ቁጥር 88 መድረሱን ዶ/ር ሊያ አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በክልሉ አምስት ዞኖች ካሉት 40 ሆስፒታሎች መካከል 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ እና 5 ሆስፒታሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በአምስቱ ዞኖች መካከል ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች መካከል ደግሞ 68ቱ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎችንም በአጭር ጊዜ ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የጤና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር፣ ኤጀንሲዎች እና የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ዶ/ር ሊያ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡ ዘገባው የኢቢሲ ነው፡፡

የካቲት 4, 2013 ዓ.ም.

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት “እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በጤና ሚኒስቴር የጋራ አዘጋጅነት ተካሄደ

የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተሳፈተፉበት የንቅናቄ ማስጀመርያ ተቋማት ማስክ ላደረጉ ብቻ አገልግሎት በመስጠት ሰራተኞችም ሆኑ ተገልጋዮች የእጅ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ በማስገንዘብ ከንቅናቄው ጎን እንዲሰለፉ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳስበዋል፡፡፡፡

ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራን እና አስተዳዳሪዎች፣ እያንዳንዱ ተማሪ ማስክ ማድረጉን ከመከታተልም ባለፈ፣ ተማሪዎች የእጅ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ፣ የህመም ምልክት ያለባቸው ካሉ፣ የባለሙያ እርዳታ እንዲያገኙ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ማስክን በተገቢው መንገድ እና በተገቢው ቦታ በማድረግ ሁሉም የንቅናቄው ተሳታፊ በመሆን ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ቀውስ ለመግታት፣ የድርሻውን እንዲወጣ፣ ሚንስትሯ አሳስበዋል።

የ”እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” ንቅናቄ ለመጪዎቹ ስድስት ወራት እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡

ጥር 6, 2013 ዓ.ም.

ሱዳን ባልረባ ፖለቲካዊ ጥምረት ኢትዮጰያን የሚጎዳ ተግባር እየፈጸመች ነው ተባለ

ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደሚጠቅማት ብታውቅም ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥምረት ምክንያት ከወዳጅ አገር የማይጠበቅ ተግባር በኢትዮጵያ ላይ እየፈፀመች መሆኑን ዶክተሩ አስታውቃዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህድስና መምህር ዶክተር ይልማ ስለሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ሱዳን የህዳሴውን ግድብ ጎርፍ በመከላከላከልና ኤሌክትሪክ ኃይል በአነስተኛ ዋጋ እንድታገኝ በማድረግ ረገድ እንደሚጠቅማት ብታውቅም ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ፖለቲካዊ ትብብር ምክንያት በድርድሩና በድንበር አካባቢ ከወዳጅ አገር የማይጠበቅ ተግባር እየፈፀመች ነው።

ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ሆነ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ እየሠራች ያለችው ሥራ ከወዳጅ አገር የሚጠበቅ አይደለም ያሉት ዶክተር ይልማ በግድቡ ድርድር ላይ ሱዳንና ግብፅ የሚያሳዩት ተለዋዋጭ ባህሪ በአጋጣሚ ሳይሆን በፈጠሩት ፖለቲካዊ ትብብር መሆኑን አመልክተዋል።

ድርድሩ የሚካሄደው በግብፅና በሱዳን ጥያቄ መሰረት በታችኛው አገራት መተማመን ለመፍጠር ሲባል እንጂ ኢትዮጵያ ፈልጋው አለመሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ድርድሩን እነሱ ካልፈለጉት ይቀጥል ብላ የምትጠይቀው ምክንያት አይኖርም፤ በህግም የመደራደር ግዴታ የለባትም፣ ግድቡንም ውሃ ስንሞላና ስናስተዳድር ተቀባይነት ባለው ዓለም አቀፍ ህግ መሰረት እንደሆነም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የታችኛዎቹን የአባይ ተፋሰስ አገራት ለመጉዳት አስባ አታውቅም፤ በጋራ እንልማ ነው የምትለው ያሉት ዶክተር ይልማ ፤ይህን የማይቀበሉ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ኢትዮጵያም በአባይ ውሃ ፍትሐዊ የመልማት መብቷንም አሳልፋ እንደማትሰጥ መታወቅ አለበት ብለዋል።

ጥር 6, 2013 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ከዳያስፖራው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰቡን አስታወቀ

ለሕይወት አድን የህክምና ቁሳቁሶች የሚውል የእርዳታ ፈንድ ማቋቋሙንም ይፋ አድርጓል።

ከ93 አገራት ከ26 ሺህ በላይ ለጋሾች በማሰባሰብ፣ 48 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ምዕራፎችን በማቋቋምና በተለያዩ መስኮች የሚያገለግሉ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እስካሁን ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ማሰባሰቡን አስታውቋል።

ከዚህም ውስጥ በትረስት ፈንዱ የምዘና መስፈርት መሰረት ለገንዘብ ድጋፍ ብቁ ለሆኑ አምስት የልማት ሥራዎች ፋይናንስ ለማድረግ 1 ሚሊዮን 342 ሺህ ዶላር ያጸደቀ ሲሆን ፕሮጀክቶቹን ለመጀመር 165 ሺህ 939 ዶላር መለቀቁን አመልክቷል።

በተጨማሪም በሂደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች እና መመዘኛዎች ሲያሟሉ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስታውቋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አስቸኳይ ፍላጎቶች ግምት ውስጥ በማስገባት የሕክምና ተቋማትን ለማገዝ ለሕይወት አድን የሕክምና ቁሳቁሶች መግዣ የሚውል የ500 ሺህ ዶላር የሕክምና እርዳታ ፈንድ ማቋቋሙንም ነው የገለጸው።

ተጨማሪ 500 ሺህ ዶላር ከለጋሾች በማሰባሰብ የፈንዱን መጠን በአጠቃላይ ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ የሚያስችል ዘመቻ መጀመሩን ጠቁሟል። ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡

ታህሳስ 23, 2013 ዓ.ም

በወርቅ ላይ ከ20 እስከ 29 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ

ጭማሪው ያስፈለገው በህገወጥ መንገድ በጥቁር ገበያ የሚሸጠውን የወርቅ ምርት ለማስቀረት ነው የጠባለ ሲሆን
በብዛት በባህላዊ መንገድ እየተመረተ የሚገኘው የወርቅ ማእድን አብዛኛው ምርቱ ወደ ብሄራዊ ባንክ ሳይደርስ በጥቁር ገበያ እየተሸጠ እንደሚገኝም ተገልጾል፡፡

ይህንን ህገወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና አምራቹ ቀጥታ በተሻለ ዋጋ ለብሄራዊ ባንክ ምርቱን እንዲያቀርብ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ባቀረበው የፖሊሲ ማበረታቻ ጥናት መሰረት ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገልጸዋል፡፡

የውጪ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ብሄራዊ ባንክ ወርቅ ለመግዛት ይገደዳል ያሉት ሚኒስትሩ በተሻለ ዋጋ ወደ ውጪ መላክን ብቻ ሳይሆን የላብራቶሪና የወርቅ ማጣራት አቅምን በመገንባት በቂ ክምችት መያዝ እንደሚያስፈልግም መጥቀሳቸውም አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል፡፡//

ታህሳስ 22, 2013 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ቁጥር በማሻቀብ ላይ መሆኑን አስጠነቀቁ

ጠቅላይ ሚንስትቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት መልዕክት የጽኑ ህሙማን ክፍል ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

አክለውም ”በዚህ ወቅት፣ በፍጹም የጥንቃቄ ርምጃዎችን ቸል ልንል አይገባም። የራሳችንን ሕይወት እንታደግ፣ የሌሎችንም ሕይወት እናትርፍ! የአፍ እና የአፍንጫ ጭንብሎችን በአግባቡ በመጠቀም የጤና ባለሞያዎቻችንን እናግዝ” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ታህሳስ 20,2013 ዓ.ም