digital marketing for government offices

የመንግሥት ተቋማት በዲጂታሉ ዓለም – ክፍል አንድ

 

የመንግሥት ተቋማት እንደየመጠኑ ይለያይ እንጂ ህዝብን ለማገልገል የተመሰረቱ ተቋማት ናቸው ስለሆነም ህዝብን ለማገልገል የሚደረገውን ጥረት ምቹ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ ወቅቱ የሚያስገድደውን የዲጂታል ዓለም መቀላቀል እና መጠቀም እንዳለባቸው ጥያቄ የለውም። የተቋማቱን አገልግሎት በድረ ገጾች እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማስተዋወቅ ዕቅዶች እና ዘመቻዎችን በአግባቡ በማብራራት ጠቃሚ መልዕክቶችን በማስፈር ብቻ ሳይሆን የሚሰጡትን አገልግሎት ጭምር በዲጂታል ስርዓት የታገዘ ዘመናዊ እና ቀላል በማድረግ ህዝቡን በምቾት በአገልግሎቱ እንዲጠቀም ያስችላል።

አንድ ግለሰብ፣ ማህበረሰብ አልያም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ለመንግስት ተቋማት ያለውን አመለካከት በመቀየሩ ረገድ የዲጂታሉ ዓለም የሚያበረክተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ብዙዎች ወደመንግስት ተቋማት ሄደው አገልግሎት ማግኘትን ግዴታ ስለሆነባቸው የሚፈጽሙት እንጂ እንደ አሰልቺ እና ቀንን እንደማበላሸት ይቆጥሩታል። ይገጥመናል ብለው የሚሰጉት የረዘመ ቢሮክራሲ ዘመናዊ ያልሆነ እና ያልሰለጠነ መስተንግዶ የረዘመ ሰልፍ እና ተራ ምቹ ያልሆነ ከባቢእና የመሳሰሉት ሰዎችን ወደመንግስት ተቋማት ስለማምራት እና ጉዳይ ስለመፈፀም ሲያስቡ ቀድሞ አዕምሮአቸውን የሚቆጣጠር ጉዳይ ነው። ተቋማቱ ይህንን ምልከታ ለማስቀየር እና ከተጠቃሚዎቻቸው ጋር ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማስተካከል እርምጃ የሚጀምሩ ከሆነ የመጀመሪያው ውሳኔ በዲጂታሉ ዓለም ያላቸውን ተሳትፎ ቆም ብሎ መከለስ እና ማደስ ነው።

በርግጥ ከወረዳዎች ጀምሮ በርካታ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት መጠኑ ይለያይ እንጂ በስማቸው የተከፈቱ የማህበራዊ ትስስር ገጿች አሏቸው የተወሰኑት ደግሞ ድረ ገጽ እስከመክፈት ደርሰዋል። አልፎ አልፎ የዲጂታሉ ዓለም ጠቀሜታ ገብቷቸው በበጎ ተጽእኖው መንገድ የሚጠቀሙበት እዳሉ ሆነው፤ አብዛኛው ግን  በገጾቻቸው ላይ የሚያስቀመጡት መልዕክቶች እና ልጥፎች ተመልካቹ ስለመንግስት ተቋማት ያለውን የተሳሳተ ትርክት ለማስተካከል ይቅርና ወትሮም ከመንግስት ተቋማት ከዚህ የተሻለ ነገር መች ይጠበቃል የሚያስብል ሆነው ስለሚገኙ የገጽታ ግንባታ ብልሽት ሌላኛው ተጨማሪ ጉልበት ሆነው ራሳቸውም ጠልፈው እየጣሉ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ነገሩ እንደዚህ ሆነ እንጂ ከየትኛውም የግል እና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማት በተሻለ መንግስታዊ ተቋማት ከህዝብ ጋር ያላቸውን ትስስር እና ቀረቤታ ለማጠናከር በዲጂታሉ ዘመን ያላቸውን ቦታ በጉልህ ማስመር ይጠበቅባቸዋል። በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት እና መተማመን እንዲጎመራ ለማድረግ አሰልቺ እና ጊዜ ወሳጅ ተብለው የሚታሰቡ አገልግሎቶችን በቀላሉ ለመከወን እና አስፈላጊ መረጃዎችን በቀላሉ ለማድረስ ዲጂታሉ ዓለም ከፈጠረው ዕድል የተሻለ አማራጭ የለም።

ስለሆነም መንግስታዊ ተቋማት በዲጂታሉ ዓለም ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በድጋሚ በመቃኘት ከታች የተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ስራ ሊሰሩ የተገባ ነው።

ገጾቹ በትክክል የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መሆናቸውን ማስረገጥ

በአገራችን የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሚኒስትር መስሪያቤቶች ኮሚሽን መስሪያቤቶች ፅህፈት ቤቶች እና ባለስልጣኖች ድረ ገጾች ቢኖሯቸውም ገጾቹ የተረሱ እስኪመስል ድረስ አዳዲስ ነገሮች የማይለጠፉባቸው ቢለጠፉባቸውም ትኩረት ሳቢ ባልሆኑ ነገሮች የተሞሉእንደነገሩየሚባሉ አይነት ገጾች ናቸው። ሆኖም መስሪያ ቤቱ ያከናወናቸውን ስራዎች ከመዘገብ ባለፈ አዝናኝ እና ሳቢ በሆነ መልኩ ዕቅዶቹን ተሞክሮዎቹን ከሌሎች ሃገራት ሊቀሰሙ የሚገቡ ልምዶችና ዕውቀቶቹን ተመልካቹን አሳታፊ የሆኑ መወያያ ሀሳቦቹን በፅሑፍ(Articles) በቪዲዮ እንዲሁም በምስል በተቀናበሩ መልዕክቶቹ (Graphics ) እና ሌሎች የተመረጡ መንገዶች ማቅረብ አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ገጾቹን (Facebook,twitter,Instagram…) ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመነጋገር ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ( Verified ) እና የዕውቅና ባጅ የሆነውን ምልክት() ከስሙ ጎን በማስለጠፍ ደረጃውን ከፍ ማድረግ ይገባል። በመቀጠልም በየጊዜው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በተመረጡ መንገዶች መልዕክት በማድረስ ከህዝብ እና ከተከታይ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር ይቻላል።

የጎግል (Google) መመዘኛዎችን በመጠቀም የተከታይን ፍላጎት እና ትኩረት መለየት

በድረ ገፆች እና በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ያሉትን ተከታዮች ማንነት እና ፍላጎት መረዳት ወሳኝ ነው። የድረ ገጽ ጎብኚዎችን ማንነት ዘመኑ በፈጠረው የቴክኖሎጂ አማራጭ መለየት ለቀጣይ ስራ ቁልፍ እርምጃ ነው። እነማን ገጹን እየጎበኙ ነው? በየትኛው የዕድሜ ክልል ይገኛሉ? በምን አይነት መሳሪያ (ሞባይል ኮምፒውተር ታብሌት )ተጠቅመው ገፁን እየጎበኙ ነው? የትኛውንድረ ገጹን ክፍል ደጋግመው ይጎበኛሉ? እና መሰል ጥናቶችን በማድረግ ለገጹ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን መለየት ይቻላል። በተጨማሪም ድረ ገጹ ላይ መረጃ ማፈላለጊያ (Search button ) በማካተት የማህበረሰቡን ፍላጎቶች መገንዘብ ይቻላል። በእነዚህ የጥናት ውጤቶች ላይ መሠረት በማድረግ የድረ ገጹን ይዘት ማሻሻል ብሎም ተቀባይነቱን መጨመር ይገባል።

ከዚህ አንጻር ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ለመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ማርኬቲንግ ውጤታማነት በተደራጀ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በመታገዝ የመፍትሄ አካል ሆኖ እየሰራ ስለሆነ፤ ከወዲሁ አብራችሁን እንድትሰሩ እንጋብዛለን፡፡ (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)

 

 

 

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top