digital marketing for government offices

የመንግስት ተቋማት በዲጂታሉ ዓለም(ክፍል 2)

የአገልግሎት ሰጪ አቀራረብን ማሳየት

የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድረ ገጽ ከአንድ አቅጣጫ ወደሌላኛው አቅጣጫ ብቻ በሚወረወሩ መልዕክቶች መታጨቅ የለበትም። ማህበረሰቡ የሚቀመጡትን መልዕክቶች ከማየት በተጨማሪ አገልግሎቶች ያስፈልጉት እንደሆነ ሊረዱት የሚችሉ አማራጮችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የድረ ገጹ የፊት ገፅ (Home page) ላይ ከሚዘረዘሩ አማራጮች ውስጥምን እናገልግልዎ?” የሚል አማራጭ በመጨመር ተቋሙ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያብራሩ እና ከፍ ሲልም በዲጂታል መንገድ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲቻል የሚያደርጉ ስርዓቶችን መዘርጋት በጣም ጠቃሚ ነው።

ዜጎች ወደድረ ገጾቹ እና ማህበራዊ ገጾቹ በብዛት እንዲመጡ መስራት

ጥሩ ድረ ገጽና ማህበራዊ ገጽ ማዘጋጀት እና ያማሩ ልጥፎችን ማጋራት መልካም ነው። ይህ ግን ጅማሮው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እነዚያ ሁሉ ነገሮች የማህበረሰቡን ትኩረት እንዲስቡ ለማድረግ መስራት ቀጣዩ አንገብጋቢ እርምጃ ነው። ህዝቡ የተለያዩ ማህበረሰቦች ስብጥር ነው። በብሔር በእምነት በትምህርት ደረጃ በዕድሜ በፆታ የተለያየ ነው። ስለዚህ እንደየአስፈላጊነቱ ማህበራዊ ሚዲያን ኤሜይል ማርኬቲንግን አጭር የፅሑፍ መልዕክት (SMS) እና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም የገጾቹን የተመልካች ፍሰት መጨመር ይቻላል።

በቀላሉ ተፈልጎ የሚገኝ ድረ ገጽ ባለቤት ለመሆን መትጋት

የአንድን ተቋም አገልግሎት ለማወቅ የሚፈልግ አንድ ግለሰብ አብዛኛውን ጊዜ የሚያደርገው ነገር እንደጉግል ያሉ መረጃ ማፈላለጊያዎች ዘንድ በማምራት ከሚፈልገው ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ቃል ጽፎ ለማፈላለግ መሞከር ነው። በዚህ ጊዜ ከፊት ለፊት የሚመጡ የመጀመሪያ ውጤቶች ግለሰቡ ከሚፈልገው መረጃ ወይም ከተጠቀመው ቃል ጋር በተያያዘ ጠንካራ ስራ የሰሩ ድረ ገጾች(well Optimized websites)ናቸው ስለዚህ አንድ የመንግስት ተቋም ከሚሰጠው ግልጋሎት ጋር በተያያዘ መረጃን ለሚፈልግ አካል በቅድሚያ ለመገኘት የሚረዱ ስራዎችን መስራት አለበት። ለዚህ ስራ የተለያዩ ስልቶች ያሉ ሲሆን የቁልፍ ቃላት (key words) በመለየት እና ስራው የሚጠይቀውን ሙያዊ ትግበራዎች በመፈፀም ገጹን የተሻለ የማፈላለጊያ ስርዓት ስኬት (SEO) እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። ለዚህም በስራው ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች እና ተቋማት ማማከር የብልህ ውሳኔ ነው።

በአጠቃላይ አንድ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በዲጂታሉ ዘመን ላይ ወደኋላ መቅረት ሳይሆን ከፊት መምራት እንዳለበት መረዳት አስፈላጊ ሲሆን የሚመሩትን ህዝብ ስነልቦና በአግባቡ በመረዳት እና ፍላጎቱን በማወቅ ዘመኑ የፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ የመተማመን ስሜትን መፍጠር ይቻላል። አገልግሎት አሰጣጥንም በማዘመን በተራዘሙ ባህላዊ የአገልግሎት አሰጣጥ መንገዶች የተሰላቸውን ማህበረሰብ ከመካስም ባለፈ ይደርስ የነበረውን መጠነ ሰፊ የመዋዕለ ነዋይ እና የጊዜ ኪሳራ ማስወገድ ተገቢ ነው።

 

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top