ዓለማችን ከጋርዮሽ ዘመን ጀምሮ እስከአሁኑ የቴክኖሎጂ ዘመን በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች እንደማለፏ ሁሉ ማርኬቲንጉም በለውጥ ሂደቱ ውስጥ አብሮ አልፏል። በዚህ ዘመን ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ የምንጠቀምባቸውን በርካታ አማራጮች ያየ የቀደመውን ትውልድ የማርኬቲንግ ዘዴዎች መፈተሹ አይቀርም። የማርኬቲንጉ መስክ በክፍለ ዘመናት ውስጥ ሊታመን የማይችል ለውጥ አድርጓል። ዘመኑ የፈጠረውን የኢኮኖሚ ስርዓት እየተከተለ በየጊዜው የተጠቃሚና የደንበኞችን ፍላጎት በመቃኘት ራሱን እያሻሻለ የመጣው ማርኬቲንግ አሁንም በለውጥ ሂደቱ እየቀጠለ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ፅሑፍ የማርኬቲንግ ሥራ ያለፈባቸውን የተለያዩ የለውጥ ምዕራፎች በመዳሰስ ስለቀጣዩ ጉዞው ጥቂት ግብአት ለመስጠት እንሞክራለን።
ምርት ተኮር ምዕራፍ (ከ1800-1920ዎቹ እ.ኤ.አ)
ይህ ዘመን መጠነ ሰፊ ምርትን መሰረት ያደረገ ምዕራፍ ነው። ድርጅቶች በብዛት የሚያቀርቡትን ምርት ደንበኞቻቸው በዝቅተኛ ዋጋ ለመግዛት ፍላጎት ያሳድራሉ ብለው ያምኑ የነበረበት ጊዜ ነው። ስለሆነም የአምራቾቹ ዋነኛ መርህ በብዛት አምርቶ ዝቅ ባለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ነበር። ይህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መነሻውን እንግሊዝ ላደረገው የኢንዱስትሪ አብዮት መነሻ ሲሆን እንደ ፎርድ ያሉ ግዙፍ ድርጅቶችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን በመቅጠር ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ምርት ማምረት የጀመሩበት ወቅት ነበር። የዘመኑ የማርኬቲንግ ስልትም ብዛት ያለውን ምርት በዝቅተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ በማቅረብ ተወዳዳሪዎችን ማሸነፍ ነበር።
ሽያጭ ተኮር ምዕራፍ (ከ1920ዎቹ-1940ዎቹ እ.ኤ.አ)
በርካታ አምራቾች ዘርፉን መቀላቀላቸውን ተከትሎ የሽያጭ ዘዴዎችና መንገዶችም በፉክክር የተሞሉበት ወቅት ነበር። በርካታ ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያው መቀላቀል የጊዜው መገለጫ የነበረ ሲሆን ድርጅቶች ከተጠቃሚና ደንበኞቻቸው እርካታ ይልቅ የሽያጭ መጠናቸው ዋነኛ የትኩረት ማዕከላቸው የነበረበት ጊዜ ነው። ፉክክሩ ድርጅቶች ለተሻለ ሽያጭ የሚረዳ ሀሳብ እንዲያውጠነጥኑ ያስገደዳቸው ሲሆን ዐይነግቡ ቅስቀሳዎችና ማስታወቂያዎች ደግሞ እንደሁነኛ መፍትሔ መታየት የጀመሩበት ጊዜ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የሽያጭ ተኮር ምዕራፍ ማስታወቂያና ቅስቀሳን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የህትመት ማስታወቂያዎች እንደ ፋሽን መቆጠር የጀመሩበት ጊዜ ሲሆን የሽያጭ ባለሙያዎች የቤት ለቤት ቅስቀሳና ምርት የማድረስን ሥራ ለዓለም በሰፊው ያስተዋወቁበት ዘመን ነበር።
ማርኬቲንግ ተኮር ምዕራፍ (1940ዎቹ-1970ዎቹ እ.ኤ.አ)
እኤአ 1940ዎቹ ኢንዱስትሪዎች በራሳቸው የሽያጭ ስኬት ላይ ብቻ ማተኮር ትክክለኛ ስልት አለመሆኑንና ደንበኞችን ለቅሬታ የሚጋብዝ መሆኑን የተረዱበት ምዕራፍ ነበር። በዚህም የማርኬቲንግ ስልቱ ትኩረቱን የደንበኞችን ፍላጎት መረዳት ላይ ያደረገ ሲሆን ይህም የእያንዳንዱን ደንበኛ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ምርትና አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በር ከፍቷል።
ዘመኑ ትክክለኛው የማርኬቲንግ ፅንሰ ሐሳብ መሰረት መጣል የጀመረበት እንደመሆኑ ድርጅቶች የገበያ ድርሻቸውን ለማስፋት የደንበኞችን ፍላጎት አብጠርጥሮ ለመረዳት የሚጥሩበትና ያንን ፍላጎት ከተፎካካሪዎቻቸው በተሻለ ለማርካት የሚተጉበት ጊዜ ነበር። የዘመኑ ማርኬቲንግ ሙሉ በሙሉ የደንበኞች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑም የደንበኛ ተኮር ምዕራፍ (customers oriented era) ተብሎ ሊጠራ ችሏል።
ተቋማት የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማወቅ በሚያደርጉት ጥናት መሠረት ለለዩዋቸው ደንበኞቻቸው እንደየፍላጎታቸው የሚሆን ምርትና አገልግሎትን ማቅረብ ለስኬት የሚያበቃ መንገድ መሆኑን በመገንዘብ ይህንኑ በተግባር ላይ አውለውታል። በዚህ ስልትም ድርጅቶቹ የእያንዳንዱን ፍላጎት ለማርካት በሚያደርጉት ጥረት ከቀደሙት ምዕራፎች የተሻለ ቁጥር ያለው ደንበኛ ለማፍራት ችለው የነበረ ሲሆን የተደራሽነታቸው ስፋትም ለላቀ ትርፍ አብቅቷቸው ነበር።
ማህበረሰብ ተኮር ምዕራፍ (ከ1970ዎቹ–እስከአሁን)
ይህ ምዕራፍ አምራቾች ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት ብቻውን በቂ እንዳልሆነና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን(Environmental Friendly) ማምረት ለሚለው ፅንሰ ሀሳብ አፅንኦት መስጠት የጀመሩበት እንዲሁም ከደንበኞቻቸው ግላዊና ወቅታዊ ፍላጎት ባለፈ የአካባቢ ደህንነትና ዘላቂ ጥበቃን ከግምት ያስገባ የማርኬቲንግ ስልት መከተል አስገዳጅ የሆነበት ምዕራፍ ነው። በ60ዎቹና 70ዎቹ በቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ሽያጭን ከማሳደግና ከትርፍ ፍላጎታቸው ባለፈ ለአካባቢያዊ ጉዳዮች የሚሰጡት ቦታ አነስተኛና የተገደበ የነበረ ሲሆን ይህም ተፈጥሮን የሚጎዳና በቀጥታ ማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርስ መሆኑ ሁሉም የተገነዘበው ጉዳይ ነበር።
የዚህ ምዕራፍ መልካም ጎን የንግድ ድርጅቶች በማህበራዊና በስነ ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ በደንበኛው ዘንድ የተሻለ ተመራጭነት እንዲኖራቸው ማስቻሉ ሲሆን ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ጎን ለጎን ለድርጅቱም ዘላቂ ዕድገት ዋስትና መፍጠር መቻሉ ነው።
የዲጂታል ማርኬቲንግ ሞዕራፍ (ከ1990ዎቹ–እስካሁን)
ይህ ምዕራፍ መላው ዓለም የማርኬቲንግ ዘርፍ ድራማዊ ሊባል በሚችል ለውጥ ውስጥ ሲያልፍ የታዘበበት ነው። የንግድ ድርጅቶች በነባሩና በተለመደው የማርኬቲንግ መንገድ ህልማቸውንና ግባቸውን እውን ለማድረግ እንደሚቸገሩ ተረድተው አዳዲስ ደንበኞችን ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ያለውን የተደራሽነት መሰናክል ለመቅረፍ አዲሱን የዲጂታል ዓለም መጠቀም ነበረባቸው።
ዲጂታሉ ዓለም የፈጠረው ዕድል ምርትና አገልግሎትን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ አዲስ የዲጂታል ማርኬቲንግ አሠራርን ያስተዋወቀ ሲሆን ከዓለም ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ በመሆኑ ገደብ የለሽ የተደራሽነት አቅም መገንባት የተቻለበት ጊዜ ነው።
ዲጂታል ማርኬቲንጉ ለአምራችና አገልግሎት ሰጪው ከፈጠረው ሰፊ ዕድል ጎን ለጎን ለተጠቃሚውም ሰፊ አማራጭ የፈጠረ በመሆኑ ደንበኞች የሚፈልጓቸውን ምርቶችና አገልግሎቶች በማመዛዘን እና በማወዳደር የሚጠቀሙበትን ዕድል አመቺ አድርጎታል።
የስማርት የሞባይል ስልኮች ገበያውን መቀላቀል የዲጂታል ማርኬቲንግ ሥራን ለማቀላጠፍ ጉልበት የሆነው ሲሆን በመስኩ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የተለያዩ ስልቶችን ለመጠቀም እድል ፈጥሯል። ይህ የዲጂታል ማርኬቲንግ ምዕራፍ ከፈጠራቸው ዘመናዊ የተግባቦት መንገዶች በተጨማሪ በርካታ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ለማህበራዊ ሚዲያ አንቀሳቃሾች፣ የድረ ገጽ ስራ ባለሙያዎች ፣ የተለያዩ የዲጂታሉ ዓለም ልጥፎች አዘጋጆች (Content Creators)፣ የሶፍትዌር መሀንዲሶችና ሌሎች መሰል ሙያተኞች በገበያው ላይ ያላቸው ተፈላጊነት እንዲጨምር አድርጓል።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የማርኬቲንግ ዘርፉ የማያልቅ የለውጥ ጉዞ መነሻውን ምርት ተኮር በማድረግ ከዚያም ወደ ሽያጭ ተኮር ሂደት አድጎ ዛሬ ላይ ምርትና አገልግሎትን ማስተዋወቅ የዘመኑ ተመራጭ ስልት አድርጎ ቀጥሏል፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን መልካም ግኑኝነትም በማዳበር ያለውን ተመራጭነት እያጠናከረ የቀጠለ ሲሆን ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል ዓለምና የተጠቃሚዎቹን ገደብ የለሽ እንቅስቃሴ ዋነኛ ግብአቱ አድርጎ በፈጣን የዕድገት ጉዞ ላይ ይገኛል።
ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽንም ዘመኑን በዋጀው አገልግሎቱ የትኛውንም የማርኬቲንግ ፍላጎትዎን ለማርካት ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቅዎ ያስታውሱ፡፡