ሎጎ የተቋምዎን ምርት እና አገልግሎት የሚወክል ስዕላዊ መገለጫ ነው፡፡ ወደ ድርጅትዎ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመጣ አዲስ ደንበኛ ቀድሞ የሚያየው የተቋሙን ሎጎ ነው፡፡ ሎጎው በደንበኛው ስሜት ላይ እንዲፈጥረው የሚፈልጉት ተጽዕኖም እንደሚመርጡት የሎጎ አይነት ይወሰናል፡፡ በፊደል አጣጣል እና በምስል ቅንብራቸው የተለያዩ ስሜቶችን እንዲፈጥሩ ታስበው የሚሠሩ ሎጎዎች በሰባት ዓይነቶች የሚከፈሉ ሲሆን ለተቋምዎ የሚሆነውን ከማዘጋጀትዎ በፊት እነዚህን ሰባት የሎጎ ዓይነቶች ቢያውቋቸው ይጠቅምዎታል፡፡
- የፊደላት ምስላዊ ቅንብር Monogram logos)
የተቋሙን ስም የመጀመሪያ ፊደላት በመውሰድና ለየት ባለ ምስላዊ ቅንብር በማዘመን የሚሰራ የሎጎ አይነት ነው፡፡ ረዘም ያለ ስም ያላቸው ድርጅቶች ይህን የሎጎ አይነት ቢጠቀሙ ይመረጣል፡፡ በስማቸው ውስጥ ያሉትን ቃላት የመጀመሪያ ፊደሎች በመውሰድ ሁለት ወይም ሶስት ፊደል ያለው፣ ከሚጠቀሙት የብራንድ ቀለምና ከተሰማሩበት ዘርፍ ጋር የሚዛመድ ገላጭ ሎጎ ማሰራት ተመራጭ ነው፡፡ እንደ ቢ.ቢ.ሲ(BBC) ፣ ናሳ(NASA) ፣ ኤች.ፒ(HP) እና አይ ቢ ኤም (IBM) የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት የሚጠቀሟቸው ሎጎዎች በዚህ መልኩ የተቀረጹ ናቸው፡፡
- የቃላት አጣጣልና ምስላዊ ቅንብር(Wordmarks)
ከላይኛው የሎጎ አይነት ጋር ተመሳሳይ ነገሮች ቢኖሩትም ሙሉ ስምን ለየት ባለ የአፃፃፍ ስርዓት(font style) እና የራስ ፈጠራ የታከለበት ምስላዊ ገለፃን በመጠቀም የሚሰራ የሎጎ አይነት ነው፡፡ የተለየ ስም ያላቸውና ያንኑ ስም ከፍ ያለ ታዋቂነት እንዲኖረው የሚፈልጉ ተቋማት የሚመርጡት የሎጎ አይነት ነው፡፡ ጎግል(GOOGLE) እና ኮካኮላ (COCA-COLA) በዚህ መንገድ የተሰራ ሎጎ በመጠቀም ምሳሌ መሆን የሚችሉ ግዙፍ ተቋማት ናቸው፡፡ በራሳቸው ለየት ያለ ስም ያላቸው ድርጅቶች ያንን ስም ባልተለመደ እና መደበኛ ባልሆነ የአፃፃፍ ስርዓት በመፃፍና የራሳቸውን ምስላዊ ቅንብር በመጠቀም በቀላሉ የማይረሳ እና በቶሎ የሚታወስ ሎጎ ባለቤት መሆን ይችላሉ፡፡ ይህንን አይነት ሎጎ ለመጠቀም በሚመርጡበት ጊዜ የሚጠቀሙት የአፃፃፍ ስርዓት ከድርጅትዎ ምርት ወይም አገልግሎት ጋር ያለውን ስነ ልቦናዊ መስተጋብር በአጽንኦት ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ለምሳሌ የፋሽን እና የመዋቢያ ዕቃዎችን የሚመርት ተቋም ቄንጠኛ እና ጥርት ያለ አፃፃፍ እንዲጠቀም ሲበረታታ መንግስታዊ ተቋማት ደግሞ የተለመደውን አፃፃፍ ደመቅ ባለ መልኩ መፃፋቸው ተመልካቹን የደህንነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል ሲሉ የስነ ልቦና ጠበብት ይመክራሉ፡፡
- ምስላዊ ምልክቶች(Pictorial marks, Logo symbols)
ደርጅትዎን ይወክላል የሚሉትን ምስል በመምረጥ የሚጠቀሙበት የሎጎ አይነት ነው፡፡ ታዋቂዎቹ አፕል እና ትዊተር ለእንደዚህ አይነቱ ሎጎ ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው፡፡ አፕል የተገመጠ የአፕል ፍሬ ያየ ማንኛውም ግለሰብ የሚያስታውሰው ተቋም ሲሆን ሰማያዊዋን በራሪ ወፍ የተመለከተ ሁሉ ትዊተርን ያስታውሳል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ያለምንም ተጨማሪ ጽሑፍ ምስሉን ብቻ የሚጠቀሙ ሲሆን ከፍ ያለ ተቀባይነት እና ታዋቂነት አላቸው፡፡ ምስል በሚመርጡበት ጊዜ ከተቋሙ ጋር እንዲያያዝ የሚያደርጉበትን መንገድ መምረጥ የሚጠበቅብዎ ኃላፊነት ነው፡፡ ለምሳሌ የዓለም የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም ከምድረ ገፅ በመጥፋት ላይ የሚገኘውን ፓንዳ እንደሎጎ በመጠቀም ስጋቱን ለሌላውም ያጋራበታል፡፡
- የፈጠራ ምስሎች(Abstract logo marks)
የፈጠራ ምስሎችን የሚጠቀሙ ሎጎዎች የሚታወቁና በቀጥታ የተወሰዱ ሳይሆኑ ድርጅቱ ሊያሳይ የሚፈልገውን መልዕክት ሊገልፅ በሚችል መልኩ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ የሎጎ አይነቶች ተቋምን ለየት ባለና በማይረሳ መልኩ መወከል ከመቻላቸው በተጨማሪ ተመልካቹ በምስሎቹ ዙሪያ ጥያቄ እንዲፈጠርበትና እንዲመራመር የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ሌላኛው ትልቁ አዎንታዊ ጎናቸው ደግሞ አንዳንድ ተፈጥሮአዊ ምስሎችና ቃላት(ፊደላት) ሊገልፁ የማይችሏቸውን ስሜቶች በፈጠራ ታግዘው መግለጻቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የናይክ ሃምፓኒ ሎጎ ነፃነትንና እንቅስቃሴን ለመግለጽ ከየትኛውም ምስል እና ጽሑፍ በላይ ተመራጭ ሆኗል፡፡ ፔፕሲና አዲዳስም የዚህን አይነት ሎጎ ምርጫቸው ካደረጉ ታላላቅ ኩባንያዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
- አኒሜሽኖችና ማስኮቶች (Animations and Mascots)
የማስኮት ሎጎዎች ስዕላዊ ገፀ-ባህሪያትን በመፍጠር የሚሰሩ ናቸው፡፡ የካርቱን እና የአኒሜሽን ባለሙያዎችን ተጠቅሞ አዝናኝና ቀለል ያሉ ምስሎችን በመስራት ገፀ-ባህሪውን እንደተቋሙ የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ የመጠቀም ጥበብ ነው፡፡ ብዙዎች እነዚህን የማስኮት ሎጎዎች የድርጅቱ አምባሳደር ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ ኬ ኤፍ ሲ(KFC) በዚህ የሎጎ ጥበብ የሚታወቅ ተቋም ነው፡፡ ይህ የሎጎ አይነት ብዙ ጊዜ ለስፖርታዊ ተቋማትና የፈጣን ምግብ (fast foods) አቅራቢ ድርጅቶች ተመራጭ ሲሆን ከቤተሰብና ከህፃናት ጋር ስሜታዊ ትስስር የመፍጠር አቅም አለው፡፡ የማስኮት እና የአኒሜሽን ሎጎዎች ከላይ ከተዘረዘሩት የሎጎ አይነቶች ጋር ሲጣመር (የፊደላት ምስላዊ ቅንብሮች ፣ የቃላት የአፃፃፍ ስርዓት ቅንብሮች ) ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል፡፡
- ተጣማሪ ምልክቶች(Combination Marks)
ከላይ የዘረዘርናቸው አምስት የሎጎ አይነቶች ተጣምረው የሚፈጥሩት ሎጎ ነው፡፡ ሁለት እና ከዛ በላይ የሆኑ የሎጎ አይነቶች እርስ በእርስ በተለያየ መንገድ ተጣምረው (ከላይ እና ከታች ተቀምጠው፣ እርስ በእርስ ተጠላልፈው ወይም ጎን ለጎን በመሆን ) አዲስ ምስልን እንዲያሳዩ ማድረግ ሲሆን እንደነ በርገር ኪንግ(BURGER KING) እና ላኮስቴ(LACOSTE) ያሉ ትልልቅ ድርጅቶች በዚህ መልኩ ይጠቀማሉ፡፡ ምስሎችን፣ የፈጠራ ምስሎችን፣ እንዲሁም አኒሜሽን እና ማስኮቶችን ከተቋሙ ሰያሜ ጋር ማጣመር በሰፊው የተለመደ በዚህ ዘዴ የተሰራ የሎጎ አይነት ነው፡፡
- አርማ (Emblems)
በተመረጠው ወይም በተዘጋጀው ቅርፃዊ ምልክት(Symbol) ውስጥ በፅሑፍ ስምን ወይም አንድን ወካይ ፊደል በማስቀመጥ የሚሰራ ሎጎ ነው፡፡ በዘመናዊው ዓለም በተለይም ሎጎዎች በትልልቅ የህትመት መጠኖች ብቻ ሳይሆን እጅግ አነስ ባሉ የቢዝነስ ካርዶች እና ቁልፍ ማንጠልጠያዎች ጭምር በሚታተሙበት ወቅት የአርማ ሎጎዎች ሊነበቡ የማይችሉበት መጠን ላይ ሊደርሱ ስለሚችሉ ብዙም ተመራጭ እንዳልሆኑ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ክለቦች፣ የእርዳታ ተቋማትና መንግስታዊ ድርጅቶች ይህን የሎጎ አይነት በመጠቀም ይታወቃሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን የሎጎ ዓይነቶች በመጠቀም የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የሚገኙ ንዑስ ተቋማት፣ ብዙዎቹ ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች እንዲሁም እንደነ ስታር ባክስ ያሉ ድርጅቶች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
አሁን ስለ ሎጎ ምርጫ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኙ ተስፋ እናደርጋለን፤ ይህም ሆኖ ሁሉም ስራ የራሱ ባለሙያ አለውና ከድርጅትዎ መለያ አንዱ የሆነውን ሎገ ለማሠራት ሲያስቡ አለያም አጠቃላይ የድርጅትዎ መለያ/ብራንድ/ ወጥና ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እንዲቀረጽልዎ ሲሹ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካካበተው እና ብቁ ባለሙያዎችን አቅፎ ከያዘው ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ጋር አብሮ መሥራትን አይዘንጉ፡፡