የዓለም ዋንጫ እና ዲጂታል ማርኬቲንግ

እ.ኤ.አ ከ 1930ዎቹ ጀምሮ በየአራት አመቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ ወዳጆች የምርጦች ምርጥ የሆነውን ሀገር ለመለየት የሚደረገውን የፊፋ የዓለም ዋንጫ በከፍተኛ ጉጉት ይከታተሉታል። የተሳታፊ ሀገራት ዜጎች የሃገራቸው ተጫዋቾች ከሌሎቹ 31 ሃገራት ጋር ተወዳድረው የሚያስመዘግቡትን ውጤት በተስፋ እንባ እና ሳቅ ታጅበው ይጠብቃሉ። ከአራት አመታት በፊት የተደረገው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ 15 ቀናት በመላው ዓለም ከ1.1 ቢልዮን በላይ ሰዎች የተመለከቱት እንደሆነ ተመዝግቧል፤ ይህ ቁጥር በተለያዩ ህዝብ ተሰብስቦ ጨዋታዎች የሚመለከትባቸው ስፍራዎች ላይ ሆነው ጨዋታዎችን የተከታተሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሳይጨምር ነው። የዓለም ዋንጫ በብዙ የመረጃ ሰጪ ተቋማት ጥናት መሰረት ብዙ ተመልካች ያለው ነጠላ ስፖርታዊ ሁነት እንደሆነ ተጠቁሟል።

የቢልዮኖች አይን በቴሌቭዥን እና በበይነ መረብ መከታተያዎች ላይ ለዓለም ዋንጫው ሙሉ ትኩረትን እንደመስጠቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የድረ ገጾች እና የበይነ መረብ ፍለጋዎች አናሳ ናቸው።ይልቁንም በርካታ ቢዝነሶች ያንን ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ያማከለ ብራንድን የማስተዋወቅ ስራ ይሰሩበታል። ለበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመክፈል ለሚሰሩ የዲጂታል ማርኬቲንግ ስራዎች ከፍ ያለ በጀት በመመደብ በሰፊው ተደራሽነትን የማጎልበት ስራ ይከውናሉ (እንደ pay per click እና Ads መሰሎቹ ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው።) በተጨማሪም ከስፖርቱ ጋር የተያያዙ ቪዲዮዎች እና ሌሎች የኮንተንት ማርኬቲንግ ልጥፎችን በማጋራት ተመልካችን እያዝናኑ ቀልቡን የመሳብ ተግባራት ውጤታማነታቸው ባለፉት የዓለም ዋንጫ ወቅቶች በጉልህ ታይቷል። የሚጠቀሙት ልጥፍ ይዘት (Content) እና የሚመርጡት ሃሳብን የማስተላለፊያ መንገድ (Platforms or mediums) እንደታላሚው አካል እና እንደአካባቢው ማህበረሰብ ፍላጎት የተቀረፁ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል።

እንደነብራዚል እና አርጀንቲና ላሉ እግር ኳስን እንደ ባህላቸው በተቀበሉ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት በ 2018ቱ የዓለም ዋንጫ ወቅት የተሰራ ጥናት እንደሚጠቁመው ወቅቱ በአካባቢው ባሉ ሃገራት ከመቼውም ጊዜ የላቀ የተጨናነቀ የድረገጽ ጉብኝት (Web traffic ) የተመዘገበ ሲሆን በተለየ ሁኔታ ደግሞ ማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ስለቡድኖቻቸው ወቅታዊ ሁኔታ ሀሳብ የሚለዋወጡባቸው መድረኮች ሚዛን ይደፋሉ።

የጎግል(Google) እና የዩቲዩብ (Youtube) የቅርብ ጊዜ ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የዓለም ዋንጫውን የሚመለከቱ ፍለጋዎች ካለፈው አመት ጀምሮ እየጨመሩ መጥተዋል።

ከታች የሚታየው ምስል የዓለም ዋንጫውን በተመለከተ የተደረጉ የጉግል ፍለጋዎችን የሚያሳይ ነው።

እንደጉግል ፍለጋ ሁሉ በዩቲዩብም የፊፋ የዓለም ዋንጫን የተመለከቱ ፍለጋዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ ቆይተዋል። የዘንድሮውን ውድድር የተመረኮዙ የዩቲዩብ ፍለጋዎች ከወዲሁ ካለፈው የዓለም ዋንጫ የ80 በመቶ ብልጫ አስመዝግበዋል። ብዙ ፍለጋ አለ ማለት ብዙ የተመልካች ቁጥር አለ ማለት እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ በታች ያሉ ሶስት ነጥቦችን መገንዘብ ብራንድዎን በወቅቱ የዲጂታል ማርኬቲንግ ስልት ተጠቅመው እንዲያጎለብቱ ያግዝዎታል።

1. የዓለም ዋንጫ ያለበይነ መረብ የሚካሄድ ቢሆንም ያለበይነ መረብ የማይደምቅበት ወቅት ላይ ነን

ምንም እንኳን ውድድሩ በአካላዊ ፍልሚያ የሚካሄድ ቢሆንም ዓለም የሚያጣጥመው ግን የኦንላይን ስርዓቶችን በመጠቀም ነው። ለዚህ ጥሩ ማስረጃው ከአራት አመታት በፊት የተደረገው የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ነው። ያንን የዓለም ዋንጫ በአካል ለመታዘብ የቻሉት 3 ሚልዮን(3,000,000) ሰዎች ሲሆኑ እነዚያን ጨዋታዎች ለመመልከት በጉግል የተደረጉ ፍለጋዎች ግን ከ 3 ቢልዮን(3,000,000,000) በላይ ናቸው። ውድድሩን የተመለከቱ የዩቲዩብ እይታዎች (Views) ደግሞ ከ 5 ቢልዮን (5,000,000,000) በላይ ሆነው ተመዝግበዋል።

የዲጂታል ማርኬቲንጉ ዓለም ምን ያድርግ?

ድረ ገጾችን እየበረበረ ካለው ሰፊ ህዝብ ጋር መገናኘት ወሳኝ ነው። በዚህ የዓለም ዋንጫ ላይ የሚኖረው የፍለጋ መጠን ካለፈው በብዙ የሚበልጥ እንደሚሆን ይጠበቃል። ስለዚህ አብዛኛው ህዝብ በፍለጋ ወቅት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ቁልፍ ቃላት (Key words) ማጥናት እና በእያንዳንዱ ልጥፎች ውስጥ ጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው።

2. የዓለም ዋንጫ ተመልካቾች 90 ደቂቃው ጨዋታ ያለፈ ነገር ማየት ይፈልጋሉ።

በዓለም ዋንጫው ከዋነኛው የቀጥታ ስርጭት ጨዋታ በብዙ ሺህ እጥፍ የበለጠ የማየት ፍላጎት በተመልካቹ ላይ አለ። 32 ሃገራት ተሳታፊ የነበሩበት የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ጠቅላላ የቀጥታ ስርጭት ሰዓት ድምር ወደ 110 ሰዓታት ገደማ ነው። ይህም ወደቀናት ሲቀየር የ5 ቀናት የእይታ ጊዜ ማለት ይሆናል። እነዚህ ጨዋታዎች ግን በዩቲዩብ ላይ ወደ 230 ሚልዮን ሰዓታት የእይታ ጊዜን ፈጥረዋል። ይህን ወደቀን ስንቀይረው ከ 26,000(ሃያስድስት ሺህ) አመታት በላይ የእይታ ጊዜ መጠን መፍጠር የቻለ ውድድር ነበር ማለት ነው።

የዲጂታል ማርኬቲንጉ ዓለም ምን ያድርግ?

በዩቲዩብ ገጽዎ ላይ የዓለም ዋንጫውን እንቅስቃሴዎች መነሻ ያደረገ ቪዲዮዎችን ማጋራት ብልህነት ነው። በተጨማሪም በእነዚህ የእይታ መጠናቸው ከፍ ባለ መገልገያ ገጾች ላይ በክፍያ መልዕክትን የማድረስ ዘዴ (paid Ads) ተጠቃሚ መሆንም የላቀ ውጤት ያስገኛል።

3. የዓለም ዋንጫ ወዳጆች የሚጋሩ ልጥፎች በልዩነት እንዲመጡላቸው ይሻሉ

የዓለም ዋንጫ ተመልካቾች ውድድሩን በተመለከተ የሚያይዋቸው ቪዲዮዎች የተለያየ ቀለም እና አይነት (content variety ) እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። አጫጭር የጨዋታውን ዋነኛ ክስተቶች የሚያሳዩ ቅንጫቢዎች (Highlights ) ፣ ታሪካዊ የውድድሩ ሁነቶች እና ክስተቶች እንዲሁም ከሻምፒዮናው ጋር ትስስር ያላቸው ሙዚቃዎች የተመልካቹን የማየት ጥም ለማርካት ቅርብ ናቸው?

የዲጂታል ማርኬቲንጉ ዓለም ምን ያድርግ?

የዲጂታል ማርኬቲንግ ባለሙያዎች በዓለም ዋንጫ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ተያያዥ ዘገባዎች እና አዝናኝ ታሪኮችን በማዘጋጀት የጎብኚ ቁጥርን ወቅታዊ ሁኔታን ተገን በማድረግ ማሳደግ ይችላሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top