ወደአንድ የመፅሓፍት መሸጫ መደብር ጎራ አሉ እንበል። በመደብሩ ካሉ በርካታ መፅሓፍት መካከል የፊት ገፁ የማረክዎትን አንድ መፅሓፍ አነሱ ። የመፅሓፉ የፊት ገፅ(cover page) ውብ መሆኑ የማንበብ ስሜትዎን ከፍ አድርጎት ወደውስጠኛው የመፅሓፉ ክፍል ሲገቡ ግን በባዶ ገፆች የተሞላ የወረቀት ስብስብ ብቻ ቢያገኙስ?
ይህን ምሳሌ ይዘን ወደርዕሳችን እንምጣ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ተቋም ሎጎ እና ብራንድ መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ ባለመሆኑ ሁለቱን ቀላቅሎ የመጠቀም ነገር ይስተዋላል። ሆኖም በብራንድ እና በሎጎ መካከል ያለው ልዩነት ልክ ከላይ እንደሰፈረው የመፅሐፍ ምሳሌ የጎላ ነው።
ብራንድ
ብራንድ ሎጎ አይደለም! ምርት ወይም አገልግሎትም አይደለም። ተቋማት ለተጠቃሚያቸው የሚገቡት ቃል ኪዳን እንዲሁም መሪ ቃልም አይደለም። ብራንድ ማለት አንድ ተቋም በምርት ወይም በአገልግሎቱ ፣ በማስታወቂያው ፣ ለማስታወቂያዎቹ በሚጠቀመው ድምፅ እና ቀለም ፣ በሎጎው ፣ በስሙ ፣ በሰራተኞቹ መገለጫዎች( አለባበስ ወዘተ) ፣ በስራ ቦታው አቀማመጥ እና የአሰራር ስርዓት እና በመሳሰሉት ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችና እርምጃዎች የሚገነባው ድምር ውጤት ነው። የእነዚህ ሁሉ ግብአቶች በተጠቃሚው(Customers )እና በእጩ ተጠቃሚው(prospect customers )ወይም በተመልካቹ(audience ) ላይ የሚፈጥረው ድምር አካላዊ እና ስሜታዊ ተፅዕኖ ብራንድ እየተባለ ይጠራል። ለአንድ ተቋም ብራንድ ሁሉ ነገሩ ነው ፤ ብራንዱን ማሳደግ ማለት ተቋሙን ማሳደግ ማለት ነው። አንድ ግለሰብ ስለዚያ ተቋም በሚያስብበት ጊዜ የሚፈጠርበት ስሜት ብራንድ ተብሎ ሊገለፅ ይችላል።
ሎጎ
በብራንድ ጥላ ስር የሚገኝ አንዱ የድርጅትን ወይም የተቋምን መወከያ መንገድ ነው። ወይም ደግሞ የዚያ ብራንድ የእይታ መለያ(Visual identity) ነው ብሎ መግለፅ ይቻላል። በውድድር በተሞላ ዓለም ውስጥ የአንድን ተቋም ብራንድ በቀላሉ እንዲወክል የሚቀመጥ ምልክት ነው። ሎጎ በተቻለ መጠን ቀለል ያለ እና ውስብስብ ገፅታን ያልተላበሰ ሆኖ ፈጠራን በመጠቀም የሰው ልቦና ውስጥ በቀላሉ ሊታወስ እንዲችል ተደርጎ ሊነደፍ ይገባል። አንድ ግለሰብ ያንን ሎጎ በሚመለከትበት ጊዜ ከሎጎው ጀርባ ያለውን ግዙፍ ብራንድ እንዲያስታውስ ማድረግ የሎጎው ተቀዳሚ ዓላማ ነው። ብዙ ጊዜ አንዳንድ ተቋማት የሎጎ ዲዛይናቸውን በመቀየር ብቻ ፣ወይም ጥሩ ሎጎ ስላላቸው ብቻ ብራንዳቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚችሉ ያስባሉ። ሆኖም ይህ ፍፁም ስህተት እንደሆነ መረዳት ይገባል።
ለዚህም እንዲረዳን በመግቢያችን ላይ ያስቀመጥነውን የመፅሓፍ ምሳሌ እንጠቀም። መፅሓፉ እንደአንድ ብራንድ ፣ የፊት ገፁን ደግሞ እንደሎጎ መውሰድ ይቻላል። የፊት ገፁ ጥሩ መሆን መፅሐፉን ምርጥ መፅሓፍ አላደረገውም። ደራሲ በቅድሚያ የመፅሓፉ ይዘት ላይ እንደሚጨነቅ ሁሉ ተቋማት ብራንዳቸውን ከፍ ለማድረግ ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ሊሰሩ ይገባል።
መፅሓፍን ተወዳጅ፣ የማይረሳ እና በገበያው ላይ ተመራጭ የሚያደርገው ጥሩ የፊት ገፁ ብቻ ሳይሆን ይዘቱ እንደሆነው ሁሉ ተቋማትም በደምበኛቸውና በእጩ ደንበኛቸው አዕምሮ ውስጥ የሚያስቀምጡት ምስል ለተመራጭነታቸውና ለተወዳጅነታቸው ባለትልቁ ድርሻ ይሆናል።
ደራሲው በመጨረሻ የመፅሐፉን ይዘት ካጠናቀቀ እና ካጠናቀረ በኋላ ያንን ሃሳብ ሊገልፅለት የሚችል የፊት ገፅ (የሽፋን ገፅ) እንደሚያዘጋጅ ሁሉ ተቋማትም የበለፀገ ብራንዳቸውን በቀላሉ ሊገልፅ የሚችል ሎጎ ሲያዘጋጁ ስራው ምሉዕ ይሆናል።
የሎጎ የብራንድን ልዩነት በተጨባጭ ምሳሌ ለማብራራት ያክል “ፌስቡክ” የተባለውን የማህበራዊ ትስስር ገፅ እንመልከት። ፌስቡክ በባለሰማያዊው “f” ሎጎው ይታወቃል። ከሎጎው ጀርባ ግን የዓለማችን ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ተቋሙ በሚሰጠው የአገልግሎት ምቾት ፣ በሚመርጠው ነጭ እና ሰማያዊ ቀለም ፣ “What is on your mind?” በሚለው ጥያቄው ፣ በ Notification ድምፁ ፣ በተለያዩ አዳዲስ የ IMOJI እና ሌሎች ፈጠራዎቹ እንዲሁም በታዋቂ ሎጎው ስሙን ገንብቷል።