የአትክልት ፍራፍሬና አበባ ምርቶችን የሚያጓጉዝ የቀጥታ በረራ ከባህር ዳር ቤልጅየም ተጀመረ

 የአትክልት ፍራፍሬና አበባ ምርቶችን የሚያጓጉዝ የቀጥታ በረራ ከባህርዳር ቤልጅየም ተጀመረ ጥር19/2010

 የአትክልት ፍራፍሬ እና አበባ ምርቶችን ለአለም ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ከባህር ዳር ቤልጅየም የቀጥታ በረራ ተጀመረ።ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ወደ አውሮፓዋ መዲና ቤልጅየም የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን የማጓጓዙ ስራ ትናንት በይፋ ተጀምሯል።በረራው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል በሳምንት ሶስት ቀን ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ ከባህር ዳር ቤልጅየም ቀጥታ የሚደረግ ነው።

በዚህም ምርቶቹ እንግልት ሳይደርስባቸው ትኩስ እንደሆኑ ለአለም ገበያ እንዲደርሱ ይረዳል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤልጅየም በተደረገ በረራም በባህር ዳር እና አካባቢዋ በጣና ፍሎራ፣ ኢትዮ አግሪ ሴፍት እና ቆጋ ቬጅ የለማ 45 ቶን ምርት ለአውሮፓ ገበያ ቀርቧል።

የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሸን የፕሮሞሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነዉ አለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ከዚህ ቀደም ምርቶችን ለአለም ገበያ ተደራሽ ለማድረግ በጉዞ ሂደት ብዙ እንግልት ይደርስ ነበር።

ምርቶቹን ከባህር ዳር አዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ወደ አለም ገበያ ለማድረስ በሚደረገው ሂደት ለብክነት ይጋለጡ እንደነበርም ተናግረዋል።

በክልሉ አሁን ላይ 16 ባለሀብቶች የአበባ ፍራፍሬና አትክልት ምርቶችን ለማምረት 1 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ከእነዚሀ ውስጥ ስድስቱ ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል ብለዋል።

በረራው መጀመሩ ለክልሉም ሆነ ለሃገሪቱ ኢንቨስትመንት መስፋፋት በተለይም ባለሃብቶችን በመሳብ በኩል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል።

አሁን ላይም ክልሉ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ተጨማሪ 800 ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

ምንጭ፡-ኤፍ ቢ ሲ

 

 

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper