በጎንደር ከተማ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ 250 ሄክታር የግንባታ ቦታ ተዘጋጀ

 

በጎንደር ከተማ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ 250 ሄክታር የግንባታ ቦታ ተዘጋጀ

 መስከረም 4/ 2010

በጎንደር ከተማ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ 250 ሄክታር የግንባታ ቦታ መዘጋጀቱን የከተማው ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ገብረእግዚአብሔር እንደተናገሩት፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን ሰሊጥና ጥጥ በግብአትነት ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ በሰሊጥ ማቀናበሪያና በምግብ ዘይት ማምረት እንዲሁም በማምረቻው ዘርፍ በጨርቃጨርቅና አልባሳት የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን ያስተናግዳል፡፡

ፓርኩ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር እስከ 200 የሚደርሱ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከተከለለው ቦታ "ዓባይ አክሲዮን ማህበር" በ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የሚውል 20 ሄክታር መሬት መረከቡን አቶ አስፋው ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የመብራት፣ የውሃና የስልክ አገልግሎቶች ለማሟላት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ምክትል ኃላፊው የገለፁት፡፡

"ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከተከለለው ቦታ ለተነሱ ሰዎችም የካሳ ክፍያ እየተመቻቸ ነው" ያሉት ምክትል ኃላፊው፥ እስካሁን ለተለቀቀው 30 ሄክታር ቦታ መንግስት 9 ሚሊየን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል።

አቶ አስፋው እንዳሉት፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ሲጀምር የሀገሪቱን የወጪ ምርትና የውጪ ምንዛሬ አቅም ከማሳደግ ባለፈ፥ ከ20ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር የከተማውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያፋጥናል፡፡

በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ ከዚህ ቀደም በተቋቋሙ አራት የኢንዱስትሪ መንደሮች ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት 5 ሚሊየን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለማስፋፋት 7 ሚሊየን ብር የካሳ ክፍያ በማከናወን 20 ሄከታር መሬት መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ አስፋው፥ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ መንደሮቹ 171 ባለሀብቶች መሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡

ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማምረቻ የሚውል አራት ሄክታር የሼድ መገንቢያ ቦታም ተከልሏል ነው ያሉት፡፡

በጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት ፖሊሲው ተግባራዊ በሆነባቸው ዓመታት ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ፥ 507 ባለሀብቶች በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በግንባታ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መሰማራታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያሳያል፡፡

ምንጭ ፡-ኤፍ ቢ ሲ

 

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper