የጉዞ ማስታወሻየክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጉጂ

ቀን 1
ነሃሴ 20/2013 ዓ.ም ማክሰኞ ሌሊት 11 ሰዓት የዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ቢሯችን የሚገኝበት ቢፍቱ አዱኛ ህንጻ ስር ተገናኝተናል፡፡ ሁሉም ክረምቱን በማገናዘብ ከአለባበሱ ጀምሮ 600 ኪሎ ሜትር አቋርጦ ጉጂ ዞን ለመግባት በስነልቦና ዝግጁ ነበር፡፡ ከእህት ኩባንያዎቻችን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ዋልታ ሚዲያና ኮምንኬሽን አመራሮችና ሰራተኞች ጋር ሲደመር 55 የሚጠጋ ሰው ለዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ነበር፡፡ ከንጋቱ 12፡00 ላይ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ በጉዟችን የኦሮሚያንና የሲዳማን ክልሎችና በውስጣቸው ያሉ ከተሞቻቸውን እያቋረጥን ተፈጥሮን ፣ በሉላዊነት ያልተበረዘ ቱባ ቱባ ባህልንና ልዩ ልዩ የአኗኗር ዘይቤን እያደነቅን ለቁርስና ለምሳ ከወሰድናቸው ጊዜያት ባሻገር ቀኑን ሙሉ ስንጓዝ ውለን ከቀኑ 11፡30 አካባቢ የድሮዋ ክብረ መንግስት የአሁኗ አዶላ ወዩ ከተማ ደረስን፡፡ ጠዋት ስንነሳ ነጌሌ ከተማ ገብቶ ለማደር አቅደን የተነሳን ቢሆንም ድካምና የአየር ንብረት ጭጋጋማ መሆን ተደምሮበት በምሽት መጓዙ አስፈላጊ ስላልነበር አዶላ ወዩ ከተማ ማደራችን እርግጥ ሆነ፡፡ አዶላ ወዩ በጉጂ ዞን የምትገኝ ትንሽ የማትባልና እያደገች ያለች ባለተስፋ ከተማ ናት፡፡ ነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀብሎ በፍቅር ማስተናገድን ያውቁበታል፡፡ በየአየር ንብረቱ ሳቢያ ልብስ አጥቦ ማድረቅ አስቸጋሪ ስለሆነ ቅዝቃዜው ያልለቀቀው አንሶላ ላይ መተኛት ግድ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ አጋጣሚ ለእግራቸው ካልሲ፣ ለጭንቅላታቸው የሹራብ ኮፊያና ሙሉ ቱታቸውን አድርገው በረኛ መስለው ሌሊቱን ያሳለፉ ተጓዦች እንደነበሩም ታዝበናል፡፡ ጠዋት በየክፍላቸው ስናንኳኳ የታዘብነው አንዱ የሳቅ ምንጭ ነበር፡፡ በተነጻጻሪም አልጋ አጥተው ተዳብለው ያደሩም እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል፡፡ ብቻ ጥቃቅን የጉዞ ተግዳሮቶች ካልሆኑ በስተቀር ከአላማችን የሚያናጥቡን ችግሮች ግን አላጋጠሙንም ማለት ይቻላል፡፡
ቀን 2
ነሃሴ 21/2013 ዓ.ም ረቡዕ ከንጋቱ 11 ሰዓት ሁሉም ተጓዥ በየመጣበት መኪና ውስጥ ገብቶ ስለአዳሩ እያወጋ ጉዞ ለመጀመር ዝግጁ ነው፡፡ ጉዞ ወደ ነጌሌ፡፡ ሁላችንም ከተሰባሰብን በኋላ ከሰባት በማያንሱ ትንንሽና ትልልቅ ተሸከርካሪዎች ተጭነንና በመስመር ተከታትለን ጉዟችንን ጀመርን፡፡ የጉጂ ዞን በተፈጥሮ ሃብቶች ከታደሉ የሃገራችን ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ በግራና በቀኝ እያየን የምናልፈው ጥቅጥቅ ያለ ደን አይንን የመሳብና መንፈስን የማደስ ትልቅ ሃይል አለው፡፡ ይህ አካባቢ የኢትዮጵያችን አንዱ ሳንባ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ የተነሳም አካባቢው ደመናና ዝናብ አያጣውም፡፡ ብን ብን የሚለው ዝናብ ፊታችሁ ላይ ሲያርፍ ቀጥሎ ልብሳችሁ እንደሚበሰብስ ፈጽሞ ወደ አዕምሯችሁ አይመጣም፡፡ ከአዶላ ነጌሌ ለመድረስ የአየር ንብረቱ ጸሃያማ ቢሆን እንኳን ከአንድ ሰዓት በላይ ማሽከርከር ይጠይቃል፡፡ ርቀቱም ከ 100- 120 ኪሎ ሜትር ሊደርስ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ መንገድ ያሰበ በጠዋት እንደሚሉት አበው …መንጋውን ተከትሎ እንደሚነጉድ የጉንዳን ሰራዊት ተከታትለን ነጌሌ ገባን፡፡
ነጌሌ ስንደርስ የዞኑና የወረዳው እንዲሁም የከተማው አመራሮች በቁጥር በርከት ብለው አቀባበል አደረጉልንና ቀጥታ ወደ መጣንበት አላማ ተቀላቀልን፡፡ 600 ኪሎ ሜትር አቋርጠን ከሄድንበት አላማ አንዱ የከተማ ጽዳት ነበረና የተዘጋጀልንን መጥረጊያ፣ አካፋና ዶማ ይዘን የጽዳት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እራሳችን የጽዳት ስራውን በተግባር በማከናወን አስጀመርን፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ከጎናችን በመሆን ያደረገው ትብብርም የሚበረታታና ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ የኛ እዚህ መገኘት ትርጉሙ በርካታ ነበር፡፡ አንደኛ የጉጂ ዞን የኢትዮጵያችን አንድ አካል በመሆኑና የጉጂም ህዝብ ወንድም ህዝብ በመሆኑ ያለንን ተቆርቋሪነት ለማሳየት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ በጥልቀት ከታሰበበት አረንጓዴ አሻራን ማኖር፣ ጽዱ ከተማን መፍጠርም ይሁን አቅመ ደካሞችን መርዳት በርቀት የማይገደብ መሆኑን ለማሳየት ከመሆኑም በላይ ከተባበርን የዜጎችን አኗኗርም ይሁን የሃገራችንን ገጽታ መቀየር እንደምንችል ለማሳየትና አርአያ ለመሆን ነው፡፡
የጽዳት ስራችንን ካጠናቀቅን በኋላ እዚያው ነጌሌ ከተማ ውስጥ ረጂ ቤተሰብ የሌላቸውን የሁለት አቅመ ደካማ አዛውንቶችን ቤት እድሳት በማስጀመር የበጎ ፈቃድ ስራችንን አከናውነን ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ ወደ መጣንበት የአዶላ ወዩ ከተማ ተመልሰናል፡፡ በነጌሌ ቆይታችን የህዝቡን እንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት በጉልህ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በዚያ ካፊያ ውስጥ ያበላችሁን ትኩስ የሚጣፍጥ የቤት ሽሮ እና ትኩስ ባለቅመም ሻይ የነበረውን ጣዕም መግለጽ ያቅተኛል፡፡ ምክንያቱም በንጹህ ልብና በፍቅር የተሰራ ነበረና፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለዞኑና ለከተማው አስተዳደሮች አብራችሁን ለነበረው ጊዜና ለመስተንግዷችሁ ምስጋናችንን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
ቀን 3
ነሃሴ 22/2013 ዓ.ም ረቡዕ ከንጋቱ 12 ሰዓት በአዶላ ሬዴ ወረዳ ሄቦራ በርኮ ቀበሌ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ለማካሄድ ጉዟችንን ጀመርን፡፡ ከንጋት ጉዞ ጋር ተላምደናል፡፡ ይሄንን ቀን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ እኛ የምንሳተፍበትን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የሚያስጀምሩልን በባህሉና በወጉ መሰረት የዞኑ ራሶች ወይም የጉጂ ዞን አባገዳዎች መሆናቸው ነበር፡፡ ሁሉም ሰው በጉጉት ወደ ቦታው መድረስን ፈልጓል፡፡ ጥቅጥቅ ባለ የሃገር በቀል ደን የተከበበውን ይህንን አካባቢ ከውጪ ለተመለከተው ሰው የቱ ጋር ችግኝ ይተከላል ብሎ ቢያስብ ሞኝ አያስብለውም፡፡ ቦታው ላይ ደርሰን ከመኪና ከወረድን በኋላ በእግራችን የ15 ደቂቃ ዳገታማ መንገድ ተጉዘን ችግኙ የሚተከልበት ቦታ ደረስን፡፡ ከዚያ ሁሉ ጫካ በኋላ እንዲህ አይነት ገላጣ መሬት ይኖራል ብሎ ማንም አልጠበቀም፡፡ በባህሉ መሰረት ፕሮግራሙ በአባገዳዎች ምርቃት ከተጀመረ በኋላ የችግኝ ተከላውን እየተሻማን አከናውነናል፡፡ በስተመጨረሻም በምርቃት የተጀመረው ፕሮግራም በምርቃት ይጠናቀቅ ዘንድ አባገዳዎቹ ጠብ የማይለውን ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱት፡፡ ከብዙ በጥቂቱ፡-
“እኛን ብላችሁ፣ እኛን ወዳችሁ፣ እኛን አክብራችሁ ይሄ ሃገር የኔ ይሄኛው ሃገር ያንተ ሳትሉ ኢትዮጵያን አስባችሁ ይሄንን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጣችሁ ለዚህ መልካም ተግባር በመምጣታችሁ ልባችን ተነክቷል፡፡ እናንተ ዛሬ ያደረጋችሁት ለትውልድ የሚበቃ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ፈጣሪ ይስጣችሁ፡፡ እንዳሰባችሁልን ፈጣሪ ለእናንተም ያስብላችሁ፡፡ በሰላም እንደመጣችሁ በሰላም ተመለሱ፡፡”
የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ወደ 7 ሰዓት ገደማ ሲጠናቀቅ ወደ አዶላ ወዩ ከተማ ተመለስንና በከተማ አስተዳደሩ የተዘጋጀልንን የምሳ ግብዣ ተቋደስን፡፡ የጉጂዎች የፍቅር መስተንግዶ በዚህም አላበቃም፡፡ ከምሳ ግብዣው በኋላ በክልሉ ባህልና ወግ መሰረት በከተማ አስተዳደሩ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ግቢ ውስጥ ሌላ ባህላዊ የስንብት ግብዣ ተደረገልን፡፡ የክልሉን ብሎም የዞኑን ባህላዊ ትውፊቶች የሚያሳዩ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ አኗኗር የሚያስቃኙ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ የቤት ውስጥ መጠቀሚያ ባህላዊ ቁሳቁሶችና የመሳሰሉትን ካስጎበኙን በኋላ የባህሉንና የወጉን ጭኮ፣ እርጎ እና ቡነቀላ በባህሉ የማቅረቢያ እቃ ቀርቦልን ተጋብዘን በፍቅር ተሸኝተናል፡፡

ሐምሌ 27, 2013 ዓ.ም

Please follow and like us:
Follow by Email
YouTube
YouTube
LinkedIn
LinkedIn
Share