የአፍሪካ ሕብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የአህጉሩ ልዩ ልዩ ተቋማት ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ በአፍሪካ በየአቅጣጫው እያጋጠመ ያለውን የተለያየ ቅርፅ የሰላም እና ፀጥታ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ፥ የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ተፅዕኖ እና ለመቋቋም እየተደረገ ስላለው ጥረት፣ የአፍሪካ ህብረት የቀረጸው አጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሂደት፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አተገባበር እንቅስቃሴ እና መሰል ወቅታዊ አህጉራዊ አጀንዳዎችን አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚሳተፉበት 40ኛው የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ÷ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል ይመክራል።
የአስፈጻሚ ምክር ቤቱ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በሚካሔደው 35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይም ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
በ40ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የምስራቅና ደቡብዊ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሃፊን ጨምሮ በርካታ የህብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ (ኤፍ ቢ ሲ)

ጥር 25, 2014 ዓ.ም

Please follow and like us:
Follow by Email
YouTube
YouTube
LinkedIn
LinkedIn
Share