የሞጆ-መቂ-ባቱ የፍጥነት መንገድ እና በቀጣይ እውን የሚሆኑ ፕሮጀክቶች የምስራቅ አፍሪካን እና አካባቢውን የንግድ ትስስር በማቀላጠፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የላፕሴት አባል ሀገራት የልዑካን ቡድን አባላት ገልፀዋል፡፡
ልዑካኑ ይህን ያሉት በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀውን የምዕራፍ አንድ የሞጆ-መቂ-ባቱ የፍጥነት መንገድን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
በጉብኝቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እና አቶ የኋላሸት ጀመረ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፥ ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የፍጥነት መንገዱ የአዲስ አበባ-ሞያሌ-ናይሮቢ-ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል በመሆኑ የቀጠናውን ሁለንተናዊ ትስስር በማጎልበት ረገድ የላቀ ሚና ይኖረዋልም ነው የተባለው፡፡
ፕሮጀክቶቹ በአፍሪካ ቀጠናዊ ነጻ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚደግፉት መገለጹን ከመንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ (ኤፍ ቢ ሲ)