ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው ለውጥ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሠረት መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በሳፋሪኮም የኬንያ ኃላፊ ሚካኤል ጆሴፍ ከተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በቅርቡ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጀ የሚገኘው ሳፋሪኮም አባል የሆነበት የዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ እያከናወናቸው ባሉ እና ወደፊት በሚያከናውናቸው ሥራዎች ዙሪያ መክረዋል ፡፡

ዶክተር ፍጹም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደችው ባለው ለውጥ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን መሠረት በማድረግ ለተጠቃሚዎች አማራጭ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማስገኘት ገበያውን ለተፎካካሪዎች ክፍት ማድረጓን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ እየተደረጉ የሚገኙ ለውጦች ለአገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር መሠረት መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

ሚኒስትሯ የሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መምጣትም በቴሌኮም ዘርፍ ያመጣል ያሉትን ጥቅም እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያስገኛቸዋል ተብለው የሚጠበቁ የስራ እድል ፈጠራዎችን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ ኃላፊዎች የተመቻቸ የኢንቨስትመንት መስክ በጀመረው መልኩ እንዲሄዱ እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የሳፋሪኮም ከፍተኛ የልዑካን ቡድንን የመሩት የሳፋሪኮም ኬንያ ኃላፊ ሚካኤል ጆሴፍ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ገበያው ተሠማርቶ ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት እንዲያቀርብ ለሰጠው እድል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጥር 25, 2014 ዓ.ም

Please follow and like us:
Follow by Email
YouTube
YouTube
LinkedIn
LinkedIn
Share