አዲስ አበባን በአዲስ የተስፋ ብርሃን!!

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን ይመኛል፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ኢንቨስተርስ ሪሌሽን፣ የሚዲያ ፕሮዳክሽን እና ሁነት ዝግጅትን በአንድ መዕቀፍ ይዞ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ ብቸኛ ተቋም የሆነው ግዙፉ ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ኃ/የተ/የግል ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የተሰየሙትን ልዩ ልዩ የጳጉሜ ቀናት መርሃግብሮች እና የእንቁጣጣሽን ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያስተባበረ ይገኛል፡፡

ጳጉሜን አንድ የይቅርታ ቀን!

ክብርት ም/ከንቲባዋ በተገኙበት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የቀድሞ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች በሚገኙበት በሸራተን አዲስ ሆቴል ልዩ የይቅርታ መጠየቅ ሥነ-ሥርዓት ይከወናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ ህዝብ አገልጋዮች መንግስት ላሳየው የአስተዳደር ጉድለት ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡  

በከሰዓት ፕሮግራም ደግሞ ሴቶች፣ ህጻናት፣ የኪነ-ጥበብና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች በመንግስት ወይም በግል ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ አረጋዊያንን ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት የአረጋዊያንን ጉልበት መሳምና እግር ማጠብ የሚከወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

ጳጉሜን ኹለት! የአብሮነት ቀን!

ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ፣ ዘመንና ፈተና ያልሻረው የኢትዮያዊያን የአብሮነት ታሪክ የሚገለጥበት ልዩ ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡ በመላ ከተማዋ ሸገር ዳቦን የሚያከፋፍሉ ሱቆች በሙሉ አቅም ለሌላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዳቦ በነጻ ያድላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቅመ ደካሞችን፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውንና በልዩ ልዩ ችግር ያሉ ዜጎችን ለማበረታታት የቤት ለቤት ጉብኝት ከመካሄዱም በተጨማሪ ለወቅታዊው ወረርሽኝ ሲባል በለይቶ ማቆያ ያሉ ዜጎችን መጎብኘት የፕሮግራሙ አካል ይሆናል፡፡

ጳጉሜን ሶስት የአምባሰደርነት ቀን!

ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪዎች ለከተማቸው አምባሳደሮች መሆናቸውን የሚያንጸባርቁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በዕለቱ የሚከናወኑ ሲሆን በአዲስ አበባ መኖሪያቸውን ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የመልካም በዓል ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህ ዕለት ክብርት ም/ከንቲባዋ በጊዚያዊው አትክልት ተራ (ጃንሜዳ) በመገኘት ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመጠበቅ የሚያግዙ የንጽህና እና ጥንቃቄ ቁሳቁሶችን ለህብረተሰቡ ያድላሉ፡፡

ጳጉሜን አራት የምስጋና ቀን!

የኢትዮጵያዊያን የሆነው ነባሩ መመሰጋገንን የሚያስታውሱ ልዩ ልዩ ክንውኖች ለዕለቱ ተይዘዋል፡፡ ለአዲስ ዓመት ዝግጅት አቅም ለሌላቸው ዜጎች ድጋፍ ማሰባሰብ፣ ድጋፍ ማድረግና ድጋፍ ላደረጉም ምስጋናን መለገስ በምስጋና ቀን የሚከወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ በዕለቱ በዋናነት ሊመሰገኑ የሚገባቸው በተለያዩ ሞያዎች ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይመሰገናሉ፡፡

ጳጉሜን አምስት የብሩህ ተስፋ ብስራት ቀን

ሀገራችን እና ህዝቦቿ ያሳለፉትን ለወራት የዘለቀ የፈተና እና የድብርት ስሜት አራግፈው አዲስ ተስፋን እንዲሰንቁ የሚያነሳሱ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት እለት ጳጉሜ አምስት ይሆናል፡፡ ዕለቱም የብሩህ ተስፋ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን የአዲስ ዓመት ዋዜማ እንደመሆኑ በዕለቱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከናወናሉ፡፡ አዲስ ዘመን መምጣቱን የሚያበስሩ መልዕክቶችን የያዙ የፖሊስ ማርሽ ባንድ አባላት በከተማዋ እየተዘዋወሩ የሚያሰሙት ጣዕመ ዜማ የዝግጅቱ አካል ከመሆኑም በተጨማሪ በሆስፒታሎች እና በቀድሞ ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች በመዘዋወር የእንኳን አደረሳችሁ መልክቶች ይተላለፋሉ፡፡

መስከረም አንድ አዲስ ዓመት

የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች በሚሳተፉበት ክብርት ም/ከንቲባዋ አንድ መቶ ለሚሆኑ አቅመ ደካችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የምሳ ግብዣ ያደርጋሉ፡፡

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የማስተዋወቅ፣ ሁነቱን የመሰነድ እና የማስተባበር ሥራዎችን በብቁ ባለሙያዎችና የዘመኑ መሣሪያዎች በመታገዝ ይሠራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የሚከበሩትን ተከታታይ ቀኖች ስኬታማ እና ደማቅ እንዲሆኑ ልዩ ልዩ ህትመቶችንና የህትመት ዲዛይኖችን ይሰራል፤ እያንዳንዱን ዕለትና ሁነቶች የሙያ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በድምጽና ምስል ይሰንዳል! ለሁነቶቹ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ መጠን ያላቸውን መድረክና የድምጽ መሳሪያዎችና ሌሎች የቁሳቁስና የሎጀስቲክስ አቅርቦት ያከናውናል፡፡  

                                         እንኳን አደረሳችሁ!

                                     በመልካም አዲስ ዓመት!

ነሀሴ 29, 2012 ዓ.ም.

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Follow by Email
YouTube
YouTube
LinkedIn
LinkedIn
Share