በትግራይ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው!

በትግራይ ክልል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡ የጤና ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የጤና ሚንስቴር እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመሆን የቀን ተቀን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ መድሀኒቶችን እና የሕክምና መገልገያዎችን የሚያሰራጩ የመቀሌ እና የሽሬ የመድሀኒት አቅርቦት ቅርንጫፎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በክልሉ የሚገኙ የደም ባንኮች ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በነዚህ ባንኮች ለማይሸፈኑ ፍላጎቶች ከማዕከል ደም እየተላከ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል የመድሀኒትና ግብአት ስርጭት ተደርጎ ወደ ስራ የገቡ ጤና ተቋማት ቁጥር 88 መድረሱን ዶ/ር ሊያ አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በክልሉ አምስት ዞኖች ካሉት 40 ሆስፒታሎች መካከል 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ እና 5 ሆስፒታሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በአምስቱ ዞኖች መካከል ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች መካከል ደግሞ 68ቱ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎችንም በአጭር ጊዜ ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የጤና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር፣ ኤጀንሲዎች እና የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ዶ/ር ሊያ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡ ዘገባው የኢቢሲ ነው፡፡

የካቲት 4, 2013 ዓ.ም.

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Follow by Email
YouTube
YouTube
LinkedIn
LinkedIn
Share