አራት አዳዲስ ደረቅ ወደቦች ሊገነቡ ነው

 

አራት አዳዲስ ደረቅ ወደቦች ሊገነቡ ነው

የካቲት21/2010

 የኢትዮጵያ የባህር ትራንዚትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከባቡር መስመር ጋር የሚገናኙ እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በቅርብ ርቀት የሚገኙ አራት ደረቅ ወደቦች ሊገነቡ መሆኑን አስታወቀ።ድርጅቱ አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘውን የድሬዳዋ ደረቅ ወደብን ጨምሮ ወደ ፊት ሊገነባቸው ያሰባቸውን ወደቦች ከባቡር መስመር እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር እንደሚተሳሰሩ ገልጿል።

የዚህ እቅድ አካል የሆነው ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት እየተገነባ የሚገኘው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ፥ ከ75 በመቶ በላይ መድረሱን በድርጅቱ የወደብ እና ፋሲሊቲ ልማት መምሪያ ዳይሬክተር ኢንጅነር አሰፋ ወርቅነህ ተናግረዋል።

ይህን የድሬዳዋ ደረቅ ወደብን ጨምሮ አምስት ደረቅ ወደቦችን በመገንባት ከባቡር መስመር እና ከኢንዱሰትሪ ፓርኮች ጋር የማስተሳሰር ስራም ለመስራት ታስቧል ነው ያሉት።ለዚህም መቐለ፣ ወረታ፣ ኮምቦልቻ እና ሀዋሳ ከተሞች የደረቅ ወደቦቹን ለመገንባት የተመረጡ ሲሆኑ፥ ለደረቅ ወደቦቹ ግንባታ ከ91 ሄክታር መሬት በላይ እየተዘጋጀ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።ከእነዚህ ደረቅ ወደቦች መካከልም መቐለ ላይ የሚገነባው ደረቅ ወደብ ዲዛይኑ በመጠናቀቅ ላይ ስለሆነ ሙሉ በጀትም ተመድቦለታል።ከመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከባቡር መስመሩ ጋር ተገናኝቶ የሚገነባው ይህ ወደብ፥ 42 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።ለዚህ ወደብ 2 ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን፥ በዚህ አመትም ግንባታውን 60 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ነው ኢንጅነር አሰፋ የሚናገሩት።ሌላው ወረታ ላይ ይገነባል ተብሎ እቅድ የተያዘለት ወደብ አንዱ ሲሆን፥ 20 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።የዚህ ወደብ የዲዛይን ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፥ ወደቡ እስከሚገነባ ድረስም ጊዜያዊ ወደብን በማቋቋም ስራው የሚጀመር ይሆናል።26 ሄክታር ላይ የሚገነባው የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የዲዛይን ስራው በዚህ አመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ለዚህ ወደብ ስራ ማስጀመሪያም 6 ሚሊየን ብር በጀት መያዙን ነው ኢንጅነር አሰፋ የገለፁት።በተመሳሳይ በሶስት ሄክታር ላይ የሚያርፈው የሃዋሳ ደረቅ ወደብም የዲዛይን ስራው እየተሰራ ይገኛል።የወረታ፣ ከምቦልቻ እና ሃዋሳ ደረቅ ወደቦች አጠቃላይ ወጪም ዲዛይናቸው ሙሉ በሙሉ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የሚታወቅ መሆኑን ነው ድርጅቱ የጠቆመው። እነዚህ ሶስት ወደቦችም በቀጣይ አመት ሙሉ በሙሉ ወደ ግንባታ እንደሚገቡ ተነግሯል። የወደቦቹን ግንባታ ለማጠናቀቅም ሁለት አመት ይፈጃል ያለው ድርጅቱ፥ እነዚህ ወደቦች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ግን የሎጅስቲክ አገልግሎት በጊዜያዊነት የሚሰራ ይሆናል።

ምንጭ፡-ኤፍ ቢ ሲ

 

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper