የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የመጓጓዣ ታሪፍ ይፋ ሆነ

 

የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የመጓጓዣ ታሪፍ ይፋ ሆነ

ታህሳስ 23/04/2010

  የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የመጓጓዣ ታሪፍ ይፋ ሆነ። የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ፥ አጠቃላይ የመንገደኞችና ለእቃ ማመላለሻ ባቡሮች ታሪፍ መውጣቱን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ለመንገደኞች በኪሎ ሜትር 0 ነጥብ 68 ብር ታሪፍ የወጣ ሲሆን፥ አዳማ ድረስ በወንበር 68 ብር ሲሆን፥ በመኝታ ከላይ 91 ብር፣ በመሃል 125 እንዲሁም ከታች 137 ብር ሆኗል።

ጂቡቲ ድረስ በወንበር 503 ብር፤ በመኝታ ክፍሎች ለሚደረግ ጉዞ ደግሞ ከላይ 671 ብር፣ በመካከለኛው 922 ብር እንዲሁም በታችኛው ክፍል ደግሞ 1 ሺህ 6 ብር የዋጋ ተመን ወጥቶለታል።

ድሬዳዋ ድረስ ለሚሄዱ መንገደኞች ደግሞ፥ በወንበር 308 ብር፣ ከላይ በመኝታ 410 ብር፣ ከመካከል 564 ብር እንዲሁም ከታች ያለውን አልጋ ተጠቅመው ለሚጓዙ 618 ብር ተመን ወጥቶለታል፡፡

ልዩ የመኝታ ክፍሎችን ለሚጠቀሙ መንገደኞች ደግሞ፥ ጅቡቲ ድረስ ለሚጓዙ ከላይ 1 ሺህ 258 ብር ከታች 1 ሺህ 341 ተተምኗል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለዕቃ ማመላለሻ ባቡሮች ታሪፍ የወጣ ሲሆን፥ አንድ ቶን በኪሎ ሜትር 22 ነጥብ 5 ብር ተመን ወጥቶለታል፡፡

የዕቃ ማጓጓዣ ባቡሮች ስራቸውን ዛሬ የጀመሩ ሲሆን፥ የመንገደኞች ባቡር ደግሞ ረቡዕ ማለዳ ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።

ለቀጣዩ አንድ ወር ተኩልም በቀን አንድ ባቡር ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፥ ይህም በመስመሩ ያልተሟሉ ጉዳዮች እስከሚሟሉ ድረስ የሚቆይ ይሆናል ነው የተባለው።

በዚህ ጊዜ ውስጥም የትራንስፖርት አገልግሎቱ አንድ ቀን እያለፈ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

መንገደኞችም የመጓጓዣ ትኬቶችን በመነሻ ባቡር ጣቢያዎች ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፥ ወደ ጂቡቲ ለሚጓዙ መንገደኞችም ከጂቡቲ ኤምባሲ መግቢያ ቪዛ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተመቻችቷልም ነው ያሉት።

አሁን ላይም ለሁለት ሳምንት የሚቆይና በሁሉም የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል።

ረቡዕ ማለዳ ስራ የሚጀምረው የመንገደኞች ማጓጓዣ ባቡር አንድ ተጎታች ከ100 እስከ 120 ሰው የመጫን አቅም ያለው ሲሆን፥ አሁን ላይ 30 ተጎታች ፉርጎዎች ይገኛሉ።

የዕቃ ማጓጓዣ ባቡሮችም አሁን ላይ በጂቡቲ ወደብ የተከማቹ ኮንቴነሮችን የማንሳት ስራ እንደሚሰሩም አስረድተዋል፤ ከዚህ አንጻርም አስመጭና ላኪዎች በአገልግሎቱ እንዲጠቀሙም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር መጠናቀቅ ከነበረበት አንድ አመት ዘግይቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም በይፋ አገልግሎት የማስጀመር ስነ ስርዓት ተከናውኗል።

የባቡር መስመሩ ከተመረቀ አንድ አመት ያለፈው ሲሆን፥ ከዚያ ወዲህም የሙከራ አገልግሎት ሲያካሂድ ቆይቷል።

ምንጭ፡-ኤፍ ቢ ሲ

 

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper