የመስቀል በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ

 የመስቀል በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ

መስከረም 17/2010

የመስቀል በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላ ሀገሪቱ ተከብሮ ዋለ።

የደመራ በዓልም በመላ ሀገሪቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በትናንትናው እለት በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናን፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና የውጭ ሀገር ዜጎች በተገኙበት ነው ከ8 ሰአት ጀምሮ የተከበረው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ህዝቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ድንበር ላይ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በጠፋው የሰው ህይወት፣ የአካል ጉድለት እና የንብረት ውድመት ቤተክርስቲያኒቱ የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።

ህዝቡ ከሁሉም በላይ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን የፈጣሪን ድምፅ ዘወትር እንዲሰማም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፥ የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው ብለዋል።

ከንቲባው በዓሉ ከሚያስገኘው የቱሪዝም ጥቅም ባሻገር የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ህገመንግስቱ በሰጣቸው ነፃነት የራሳቸውን አስተምህሮና የአምልኮ ስርዓት እያስቀጠሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

መንግስት እና ሃይማኖት የተለያዩ ሆነው በሀገራዊ አጀንዳዎች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና መሪዎቿ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከመንግስት ጋር እየሰሩ በመሆናቸው ሊበረታቱ የሚገባው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሀገራችን ሃይማኖቶች ስለሰላም፣ ስለመቻቻል እና ስለልማት አስፈላጊውን ሚና መወጣታቸውን ጠቅሰው፥ ይህን በጎ ስራቸውን እንዲያስቀጥሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የሃይማኖቶች ነፃነት እና ህልውና የሚረጋገጠው የሰላም፣ የመከባበር እና የመቻቻል መኖር በመሆኑ በሃይማኖት ሽፋን የሚፈፀሙ የፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮው የመስቀል ደመራ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስ ባስልዮስ ሁለተኛ በንግግራቸው የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ በመመዝገቡ ደስታቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ አብያተ ቤተክርስቲያናት እህትማማችነት በትውልድ እንደሚቀጥልም ነው አቡነ ባስልዮስ የገለፁት።

የመስቀል ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።

ምንጭ፡-ኤፍ ቢ ሲ

 

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper