የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ 16 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል

 

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ 16 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል

ነሐሴ30/2009

የኢንዱስትሪው ዘርፍ የዛሬ 10 ዓመት ከሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ ከነበረው የ10 በመቶ ድርሻ አሁን ወደ 16 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።

በነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በየዓመቱ የ20 በመቶ እድገት እያስመዘገበች ቢሆንም በአምራቹ ዘርፍ እንደተፈለገው ለውጥ አልመጣም ተብሏል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መብርሃቱ መለስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 16 ነጥብ 6 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል።

ይህም ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው 10 በመቶ የ6 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲሉም ተናግረዋል።

ሆኖም ግን የማምረቻ ኢንዱስትሪ አሁንም ዝቅተኛ ድርሻ ነው ያለው ይላሉ ዶክተር መብርሃቱ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ የማምረቻውን ዘርፍ አሁን ካለበት 5 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 8 በመቶ እንዲያድግ እቅድ መያዙንም ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ያነሱት ዶክተር መብርሃቱ፥ የአገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን ያለመሆን እና የግብአት አቅርቦት ችግር የዘርፉ እድገት እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ ነው ሲሉም ሚኒስትር ደኤታው አንስተዋል።

የግብርና ግብአቶችን በስፋት ለማቅረብም በእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በእንሰሳት እና አሳ ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ግብርናውን ለማዘመን አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ዶክተር መብርሃቱ ገልፀዋል።

የአመራረት ሂደትን የማዘመን፣ የመስኖ ልማት ስራዎችን የማሳደግ፣ በገጠር አካባቢዎች መሰረተ ልማትን የማስፋፋት እንዲሁም ግብርና እና ኢንዱስትሪውን ለማስተሳሰር የህግ ማዕቀፎችን እና የማበረታቻ ስርአት የመዘርጋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ዶክተር መብርሃቱ አያይዘውም፥ ዘርፉ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑ አለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረጉን ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪ ልማት ለሚሊየኖች የስራ እድል ለመፍጠር የተያዘውን ግብ በአንድ ጊዜ በሁሉም ታዳጊ ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአውሮፓውያኑ አቆጣጣር 2015 በተመረጡ ሶስት ሀገራት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል።

በዚህም ከተመረጡት ሶስት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህም ሀገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እና ድህነትን ለመቅረፍ የሄደችው ርቀት ውጤት ነው ብለዋል።

ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማትን ማረጋገጠ አላማው ያደረገው የዘላቂ ልማት ግብ በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነው ሀገሪቱ ለራሷም ለሌሎች ሀገራትም ልምድ ማካፈል እንደምትችል ታምኖበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን እውን ለማድረግም ሀገሪቱ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው ሲሉም ዶክተር መብርሃቱ ተናግረዋል።

ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ

Log in

Contact us

Wafa Marketing & Promotion PLC

Mexico Biftu Building 8th & 11th Floor ,

In front of Addis Ababa University School Of Commerce

Addis Ababa, Ethiopia

Phone: +(251) 115 525031

JoomShaper